በአማራ ክልል በእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም እየተሠራ ነው።

8

 

የአማራ ክልል ያለው ተፈጥሯዊ ጸጋ ለእንስሳት እርባታ ዘርፍ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ በክልሉ የሚገኘው ሰፋፊ የወል መሬት እና የሰብል ተረፈ ምርት ደግሞ ለእንስሳት ልማት ሥራው ውጤታማነት ትልቅ አቅም ነው፡፡

በደብረ ማርቆስ ከተማ በወተት ላም እርባታ ዘርፍ የተሰማሩት ሙሉሰው ፀሐይ እና ጓደኞቹ ኢንተርፕራይዝ ከአራት ዓመት በፊት ነበር አንድ ላም ገዝተው ወደ ሥራ የገቡት። ዛሬ ላይ ግን ከ12 በላይ ዘመናዊ ላሞችን በማርባት በቀን እስከ 120 ሊትር ወተት ለገበያ እያቀረቡ መኾኑን ይገልጻሉ፡፡

ማኅበሩ ያለበት የእርባታ ቦታ መጥበብ ችግር ቢፈታለት በቀጣይ ሥራውን በማስፋፋት በወተት ምርት ላይ እሴት ጨምሮ እና አቀነባብሮ ለማቅረብ ዕቅድ እንዳለውም ተገልጿል።

ሌላው በከተማው በወተት ላም እርባታ ኢንቨስትመንት የተሰማራው ኢዲኤ የወተት ላም እርባታ ድርጅት ባገኘው ሰፊ ቦታ በቀን እስከ አርባ ሊትር የሚሰጡ የተሻለ ዝርያ ያላቸውን ላሞች በማርባት ለበርካቶች የሥራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡

ማኅበሩ የወተት እና ምጥን መኖ ማቀነባበር የሚችሉ ማሽኖችን በማስገባት እና የላሞችን ዝርያ በማሻሻል የእርባታ ሥራውን የበለጠ ዘመናዊ ለማድረግ እየሠራም ነው።

በክልሉ የእንስሳት ምርታማነትን የሚያሻሽሉ አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ሰፊ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት ለሀገር ውስጥ ግብይት በማቅረብ የተቀረጹ ግቦችን ለማሳካት በትብብር እና በአንድነት እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ጋሻው ሙጨ (ዶ.ር) ገልጸዋል።

ተፋሰስን እና የአረንጓዴ አሻራን መሠረት ያደረጉ የእንስሳት እርባታ እና የወተት ክላስተሮችን በመፍጠር ዘርፉን ለማዘመን በሚከናወኑ አሠራሮች በቢሮው የተቀመጡ የአሻጋሪ እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ አበረታች ውጤቶች እየተገኙ መኾኑን ጠቁመዋል።

በከተማው እየተከናወነ ያለውን የእንስሳት እርባታ ዘርፍ ተንቀሳቅሰው የተመለከቱት ዶክተር ጋሻው ሙጨ በየአካባቢው የሚሠራ እጅ እና የሚያስተውል አዕምሮ ካለ በክልሉ ያለው የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ሠርቶ ለመለወጥ አመች ነው ብለዋል።

በዘርፉ የወጣቶች ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱንም በመስክ ምልከታቸው ማረጋገጥ መቻላቸውን ኀላፊው ጠቁመዋል፡፡

ያለንን ሀብት አቀናጅቶ ጥቅም ላይ ለማዋል እና ምርቱን በተሳለጠ የግብይት ሠንሠለት እሴት ጨምሮ ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑንም ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በ2018 በጀት ዓመት የመኖ አማራጮችን በማስፋት እያደገ የመጣውን ተስፋ ሰጭ ውጤት በሚፈለገው ልክ ውጤት እንዲያስመዘግብ ሰፊ ምርት የሚሰጡ እና ለየአካባቢው ተስማሚ የኾኑ የእንስሳት ዝርያዎችን ተደራሽ ለማድረግ መሠራቱን የጠቀሱት ቢሮ ኀላፊው በቀጣይ ለአልሚ ባለሀብቶች እና በዘርፉ ለሚሠማሩ ወጣቶች የመስሪያ ቦታ እና ብድር በማመቻቸት የበለጠ ውጤት ለማምጣት በትኩረት እንደሚሠራ አስገንዝበዋል፡፡

በአማራ ክልል ከ46 በላይ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እንደሚገኙ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

#አሚኮ #investment #ኢትዮጵያ

#ደብረ_ማርቆስ፡ ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🌱 ” ችግኝ መትከል ብቻውን ግብ አይኾንም” ይልቁንም…..!
Next articleአዲስ ተስፋ በሀረሪ – 47 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ገቡ።