🌱 ” ችግኝ መትከል ብቻውን ግብ አይኾንም” ይልቁንም…..!

13

 

የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የችግኝ ተከላ እና የደም ልገሳ ፕሮግራም አካሂዷል።

የቢሮው ምክትል ኀላፊ ጋሻው ተቀባ ክልሉ ብዙ አበርክቶ ያላቸው የሀገር በቀል ችግኞች ጸጋ እንዳላቸው ታሳቢ በማድረግ የቢሮው አጠቃላይ ሠራተኞች ለባሕል ጥብቃ ሊኾኑ የሚችሉ ችግኞችን መትከላቸውን ገልጸዋል። በአማራ ክልል ባሕል፣ ኪነ ጥበብና ዝክረ ታሪክ ጽሕፈት ቤት እና በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግቢ ነው ችግኝ የተከሉት።

ከዚሁ ጎን ለጎን የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራትን ታሳቢ በማድረግ ከችግኝ ተከላ በተጨማሪ ደም መለገሳቸውንም ነግረውናል።

የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራ አሁን ላይ እንደ ባሕል እየኾነ ነው ያሉት ምክትል ኀላፊው ቢሮው እስከ ወረዳ ድረስ ባለው መዋቅር የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ የ90 ቀን ዕቅድ አቅዶ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በዚህም ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች መደገፍ፤ የተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ማሰባሰብ፤ ደም ልገሳ፤ የቅርስና ባሕል ጥብቃ እና እንክብካቤ ሥራዎች እየሠሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

የክረምት ስፖርታዊ ውድድሮችን የማዘጋጀት፤ በጎርፍ እና በጨዋታ ጉዳት የደረሰባቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን እና የመዝናኛ ማዕከሎች እንክብካቤ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነም አንስተዋል። እነዚህ በክረምት የሚሠሩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት የባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ሥራዎችን በመደገፍ ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ እንደኾነም አንስተዋል።

የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ሠራተኛው አበበ እምቢያለ “የሰው ልጅ ልብስ ሲለብስ እንደሚያምርበት ሁሉ መሬትም በችግኞች አረንጓዴ ስትለብስ እንደሚያምርባት” ነው የገለጹልን። የሰው ልጆች በተለያየ ምክንያት የተራቆተውን ምድር በችግኝ እንዲያገግም እና ልምላሜ እንዲኖረው ማድረግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውም አንስተዋል።

የሚተከሉት ችግኞች ዝም ብለው አረንጓዴ ለማድረግ ብቻ ሳይኾን ከዛ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዲኖራቸው ታሳቢ ተደርገው የሚተከሉ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

ቢሮው ባለፈው 2017 በጀት ዓመትም የችግኝ ተከላ እና ደም ልገሳ መርሐ ግብር ማከናወኑን አስታውሰዋል። በየዓመቱ የከተማውም ኾነ የገጠሩ ማኅበረሰብ ችግኝ ይተክላል፤ ምን ያህሉ ጸድቆ ለቀጣይ ልምላሜ በቃ የሚለውን ማረጋገጥ ግን ተገቢ መኾኑን ጠቅሰዋል።

በችግኝ ተከላ እና ደም ልገሳ መርሐ ግብሩ ያገኘናቸው ሌላኛዋ የተቋሙ ሠራተኛ ጎጃም አበበ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የተቋሙ ሠራተኛ በጋራ የተለያየ ቦታ ላይ ችግኝ ሲተክሉ እንደነበር አስታውሰዋል። ሲደረጉ የነበሩ እንክብካቤዎች ግን ውስንነት እንደነበረበት አስታውሰዋል።

በቀጣይም የተተከሉ ችግኞችን እንክብካቤ እንደሚያደርጉላቸው አረጋግጠዋል።

#አሚኮ #አረንጓዴ_አሻራ #ኢትዮጵያ

#ባሕር_ዳር ሐምሌ15_2018_ዓ_ም

✍️ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየፋይናንስ ተቋማት አካታች አገልግሎትን ተደራሽ ሊያደርጉ ይገባል።
Next articleበአማራ ክልል በእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም እየተሠራ ነው።