የፋይናንስ ተቋማት አካታች አገልግሎትን ተደራሽ ሊያደርጉ ይገባል።

14

 

የአማራ ክልል የፋይናንስ አካታችነት ክልላዊ ምክር ቤት በፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጅ ትግበራ ዙሪያ በክልሉ ከሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ተወያይቷል።

የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ እና የፋይናንስ አካታችነት ክልላዊ ምክር ቤት ምክትል ሠብሣቢ አታላይ ጥላሁን የውይይቱ ዓለማ በብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ማዕቀፍ ውስጥ የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ከክልሉ የፋይናንስ አካታችነት ግቦች ጋር ማስተሳሰር እና በጋራ የምንሠራበትን መንገድ ለመቀየስ ነው ብለዋል።

የፋይናንስ አካታችነት ለኢኮኖሚ ዕድገት፤ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለቁጠባ ዕድገት መሠረት መኾኑንም ተናግረዋል። በክልሉ ከ20 በላይ ባንኮች፤ 2 ሺህ 323 የባንክ ቅርንጫፎች እና 109 የማይክሮ ፋይናንስ ቅርንጫፎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል። ኾኖም የፋይናንስ አገልግሎት ተዳራሽነት በገጠር አካባቢ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ አለማድረጉን ነው ያነሱት።

ከተደራሽነት ባሻገር የአካታችነት ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ተደራሽነትን ማሳደግ እና ተስማሚ አገልግሎቶችን ማጠናከር የክልሉ ስትራቴጂ ትኩረት መኾናቸውን ተናግረዋል። የፋይናንስ ተቋማት አካታች የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የመረጃ ስብሰባ እና ትንተናን ማሻሻል፤ ዲጂታል የሞባይል ክፍያዎችን ማበረታታት፤ አገልግሎት ያላገኙ አካባቢዎችን ማዳረስ፤ ሴቶችን ተሳታፊ ማድረግ፤ ቁጠባን ማሳደግ፤ የማይክሮ-ኢንሹራንስ ሥርዓትን ማጠናከር ላይ ትኩረት እንደሚደረግባቸው ገልጸዋል።

የአማራ ክልል የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጅ አማካሪ አብነት በላይ በክልሉ የፋይናንስ ተቋማትን ማስፋት እና ተደራሽነትን ማረጋገጥ ላይ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።
በክልሉ ጥናቶችን በማድረግ የፋይናንስ ተቋማት ተደራሽነታቸውን ወደ ወረዳዎች እንዲያስፋፉ መንገዶችን የማመላከት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ማኅበረሰቡን ቴክኖሎጅ በማላመድ የዲጅታል ግብይት ተጠቃሚ እንዲኾን ድጋፍ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች አገልግሎቶችን ማዘመን፤ ተደራሽነትን ማስፋት፤ ቁጠባን ብቻ ሳይኾን ብድርንም ማበረታታት፤ በቅርንጫፍ ደረጃ የደንበኞችን የፋይናንስ ዕውቀት ማሳደግ፤ ለሴቶች እና ወጣቶች የተዘጋጁ ከማስያዣ ነጻ የኾኑ አገልግሎቶችን መስጠት እንደሚጠበቅም አሳስበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የዓባይ ባንክ ባሕር ዳር ዲስትሪክት የሀብት ማሠባሠብ እና የቅርጫፎች ሥራ ማሥተባበሪያ ከፍተኛ ሥራ አሥኪያጅ ሽባባው ሙጨ ተቋሙ በተለያዩ ቦታዎች ቅርንጫፎችን በመክፈት የፋይናንስ አካታችነትን ለማስፋት እየሠራ ነው ብለዋል። ማኅበረሰቡ ከጥሬ ገንዘብ ግብይት ወደ ዲጂታል ግብይት ሥርዓት እንዲሸጋገር በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

የፀደይ ባንክ የጥቃቅን እና አነስተኛ ፋይናንሲንግ ምክትል ፕሬዝዳንት አጋዤ ጌታሁን በፋይናንስ አካታችነት የገጠሩ ማኅበረሰብ እና ሴቶች ይበልጥ ተሳታፊ እንዲኾኑ ተሠርቷል ብለዋል። የማኅበረሰቡን የፋይናንስ ክህሎት ለማሳደግ ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሠሩም አብራርተዋል።

የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ ከመንግሥት ጋር በቅንጅት እንደሚሠሩም የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

#አሚኮ #የፋይናንስ_አካታችነት #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር#ሐምሌ_15_2018 ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“የሰጠነው ደም የሰዎችን ሕይወት የሚያስቀጥል በመኾኑ ደም በመለገሳችን ደስተኞች ነን” የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች
Next article🌱 ” ችግኝ መትከል ብቻውን ግብ አይኾንም” ይልቁንም…..!