234 ሺህ ደርዘን ደብተር እና 29 ሺህ ባኮ እስክርቢቶ ለነገ ተስፋዎች!

4

 

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ተቋማት እና ባለሃብቶች “አንድ ደርዘን ደብተር ለአንድ ተማሪ” በሚል መልእክት ድጋፍ እንዲያደርጉ ሲያካሂድ የቆየውን የሦስት ቀናት ንቅናቄ አጠናቅቋል።

በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ ድጋፍ ሲያደርጉ ያገኘናቸው የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቢሮ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ስሜነህ አያሌው በአቅም ማነስ እና በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ለተቸገሩ ተማሪዎች ከተቋሙ ሠራተኞች በመሠብሠብ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።

በ135 ሺህ ብር ደብተር እና እስክርቢቶ ድጋፍ ተደርጓል ነው ያሉት።

የዩኒሴፍ አማራ ፊልድ ኦፊሰር አየነው መሰለ የተቋሙ ሠራተኞች በ157 ሺህ ብር ወጭ ደብተር፤ እስክርቪቶ፣ ላጲስ እና የእርሳስ መቅረጫ ድጋፍ አድርገናል ነው ያሉት።

በመንግሥት ብቻ የሚሰጥ ድጋፍ የተማሪዎችን ችግር የሚቀርፍ ባለመኾኑ ሁሉም ተቋም ሊደግፍ ይገባል ነው ያሉት። ከደብተር ባሻገር የመማሪያ ክፍሎችን መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የአማራ ክልል ፕሮግራም ሥራ አሥኪያጅ ጌትነት ሞላ በ88 ሺህ ብር ወጭ ደብተር እና እስክርቢቶ የተቋሙ ሠራተኞች ድጋፍ አድርገዋል ብለዋል።

የተቋማቱ የሥራ ኀላፊዎች በቀጣይም ቤተሰቦቻቸው በገቢ ዝቅተኛ ለኾኑ ተማሪዎች የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን በክልሉ በገቢ ዝቅተኛ ለኾኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ የማሠባሠብ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል።

ባለሃብቶች እና ተቋማት በሦስት ቀናት ንቅናቄ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ተሠርቷል ነው ያሉት። በንቅናቄው በርካታ ባለሃብቶች እና ተቋማት ድጋፍ አድርገዋል ብለዋል።

ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በክልሉ ከሐምሌ ወር ጀምሮ 234 ሺህ ደርዘን ደብተር እና 29 ሺህ ባኮ እስክርቢቶ መሠብሠቡን አንስተዋል። የትምህርት ቢሮ ሠራተኞች በራሳቸው አቅም 10 ሺህ ደብተር ለማሠራጨት እየሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል።

ድጋፉ ተማሪዎች በቁሳቁስ እጥረት ሳይጨናነቁ እንዲማሩ የሚያስችል ነው ብለዋል። ትምህርት እስኪጀመር ድረስ ድጋፍ የማሠባሠብ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የተሠበሠበ የትምህርት ቁሳቁስ በፍትሐዊነት እንዲሠራጭ ይሠራል ብለዋል።

#አሚኮ #education #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_15_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleለሻደይ ከመሰባሰብ እስከ ልማት ማህበር ምስረታ – የዋጎች ዋልማ