
የዋግ ሕዝብ ባሕላዊ እና ማህበራዊ መገለጫ የኾነው የሻደይ በዓል፣ ከሴቶች ነፃነት እና ከትውፊታዊ ክዋኔነቱ ባሻገር የዋግ ልማት ማኅበርን (ዋልማ) በማዋለድ ለአካባቢው ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዕድገት መሠረት መጣል ችሏል ይላሉ የዋልማ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ አስተባባሪ አስራት ታደሰ።
በ2000 ዓ.ም “ሚሊኒየምን ለሻደይ” በሚል መሪ መልዕክት በዓሉ በተከበረበት ወቅት በተወሰኑ ባለራዕይ መሪዎች እና ባለሙያዎች ሀሳብ ማኅበሩ ተጠንስሶ በ2001 ዓ.ም መሥራች ጉባኤውን በማካሄድ በ2002 ዓ.ም ሰኔ ወር ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል አቶ አስራት።
አቶ አስራት ታደሰ ዋልማ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የበዓሉ ስፖንሰር በመኾን ባሕሉን እና የኽምጣና ቋንቋን ከማበልጸግ ባሻገር የሕዝቡን ዘለቄታዊ ችግሮች ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል ነው ያሉት።
ማህበሩ ባካሄደው ሀገር አቀፍ ቴሌቶን ከ381 ሚሊዮን ብር በላይ በፕሮጀክት እንዲሁም 42 ሚሊዮን ብር የሚገመት በዓይነት ሀብት በማሠባሠብ ሥራዎችን መሥራቱንም ጠቁመዋል።
ዋልማ በትምህርት ዘርፍ ከ65 በላይ ደረጃቸውን የጠበቁ አዳዲስ እና የማስፋፊያ የትምህርት ቤት ብሎኮችን ሠርቷል።
በጤና ዘርፍም 10 ዘመናዊ ጤና ጣቢያዎች እና አራት የጤና ኬላዎች ግንባታን እንዲሁም ለተቋማት አስፈላጊ ግብዓቶችን ማሟላትም ችሏል።
በቋንቋ እና ባሕል በኩልም ሦሥት የኽምጣና ቋንቋ ማጣቀሻ መጻሕፍትን አሳትሞ ለቋንቋው ዕድገት በማበርከት የራሱን ድርሻም ተወጥቷል።
በየቀበሌው የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን በማከናወን የተፈጥሮ ሀብትን ከንክኪ ነፃ ማድረግ እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል የመፍጠር ሥራም አከናውኗል።
የዋግ ተወላጆች እና ደጋፊዎች ይህንን አዎንታዊ የልማት እንቅስቃሴ አጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ባሕላዊ እሴቶችን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ከማህበሩ ጎን እንዲቆሙም ጥሪ ቀርቧል።
ዘጋቢ – አሰፋ ብርሃኑ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
