“የሰጠነው ደም የሰዎችን ሕይወት የሚያስቀጥል በመኾኑ ደም በመለገሳችን ደስተኞች ነን” የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች

10

 

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ጋር በመተባበር “በጎነት መገለጫችን፥ ደማችን ለወገናችን” በሚል መሪ መልዕክት የደም ልገሳ መርሐ ግብርን በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ደም የለገሱት ሙሉሰው ጌጡ እና ውዴ እምቢአለ ደም መለገስ በወሊድ ወቅት ደም በመፍሰስ ምክንያት ሕይወታቸውን ለሚያጡ እናቶች መድረስ በመኾኑ ለሕሊና ደስታን የሚፈጥር ተግባር ነው ብለዋል።

የሰጠነው ደም የሰዎችን ሕይወት የሚያስቀጥል በመኾኑ ደም በመለገሳቸው ደስተኛ ነን ነው ያሉት። ደም መለገስ የሚፈጥረው ምንም ዓይነት ችግር የለም ያሉት ለጋሾቹ ደም መለገስን ባሕል አድርገው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ጌታቸው ግዛቸው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 17 ዋና ዋና እና 34 ንዑስ ተግባራት አሉት ብለዋል።

በከተማ አሥተዳደሩም በኹሉም ተግባራት ሠፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውን የጠቀሱት ኀላፊው ዘንድሮ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ መጨመሩን ተናግረዋል።

በዕለቱ በከተማ አሥተዳደሩ በተለያዩ ቀጣናዎች እየተካሄደ በሚገኘው የደም ልገሳ መርሐ ግብር ማኅበረሰቡ ደሙን ለወገኑ እየለገሰ መኾኑን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ምክትል ኀላፊ ዝና ጌታቸው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በጎነትን ባሕል እና መገለጫው ያደረገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በተግባራቱ 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኅብረተሰብን በማሳተፍ 15 ሚሊዮን የሚኾኑ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ጠቁመዋል።

በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚሠሩ 17 ተግባራት መካከል የጤና ሥርዓትን ውጤታማ ለማድረግ የደም ልገሳ መርሐ ግብር በትኩረት እየተከናወነ መኾኑንም ገልጸዋል።

በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ እንደ ክልል 30 ሺህ ዩኒት ደም ለመሠብሠብ ዕቅድ ተይዟል ብለዋል። እስካሁንም ከ5ሺህ 400 በላይ ዩኒት ደም መሠብሠብ ተችሏል ነው ያሉት።

የዛሬው የደም ልገሳ መርሐ ግብርም ዕቅዱን ሊያሳካ በሚያስችል መልኩ በኹሉም የክልሉ አካባቢዎች በትኩረት እየተካሄ መኾኑን ነው የተናገሩት።

ማኅበረሰቡ የምንለግሰው ደም ካልለገስነው በተፈጥሯዊ መንገድ ከሰውነታችን የሚወገድ፥ ከለገስነው ግን ሕይወትን የሚታደግ መኾኑን ተገንዝቦ ደም መለገስን ባሕሉ ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት።

#አሚኮ #ደሜን_ለወገኔ #ሕይወትን_አትርፉ #DonateBlood #SaveLives

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም

ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየመከላከያ ሠራዊት በሰሜን ወሎ ዞን በጽንፈኛው ቡድን ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ ነው።
Next articleየፋይናንስ ተቋማት አካታች አገልግሎትን ተደራሽ ሊያደርጉ ይገባል።