
ለወትሮው ሳሙናን የምናውቀው በደረቅ፣ በዱቄት እና በፈሳሽ መልክ ነው። የባቲ ከተማ ነዋሪዋ ወጣት ኢክራም ሙሐመድ ደግሞ ሳሙናን በወረቀት መልክ አዘጋጅተዋለች።
ኢክራም ለእጅ መታጠቢያ የሚያገለግል የወረቀት ሳሙና ፈጥራለች። ወጣቷ በአካባቢዋ ካሉ ችግሮች በመነሳት የፈጠራ ሀሳቧ እንደመነጨ ትናገራለች።
የወረቀት ሳሙናው ለአያያዝ ምቹ እና በየትኛውም ቦታ እጅን ለመታጠብ የሚያገለግል ነው ብላለች። ሳሙናው ለየት የሚያደርገው በፊት ከሚታወቁት የጋራ መጠቀሚያ ሳሙናዎች በተለየ ሁኔታ በግል ለመጠቀም ምቹ መኾኑን ነው የገለጸችው።
እሷ ያዘጋጀችውን የወረቀት ሳሙና ለመሥራት ያነሳሳት በተለያዩ ቦታዎች ስትንቀሳቀስ እጅ ለመታጠብ ሳሙና አለማግኘቷ እንደኾነ አንስታለች፡፡
ሳሙናውም በአካባቢ በቀላሉ በሚገኙ ጥሬ እቃዎች እና እጅን በማይጎዳ መልኩ በራሷ ኬሚካሎችን በመቀመም የሚፈለገውን ቅርጽ በማስያዝ እንዳዘጋጀችው ነው ያጫወተችን።
አጠቃቀሙም አንድ ወረቀት በመለየት በእጅ ላይ በማድረግ መጠቀም ይቻላል ነው ያለችው፡፡ ከሌሎች የሳሙና አይነቶች የሚለየው ቦታ እና ሁኔታዎች የማይገድቡት እና ለአያያዝ ምቹ የኾነ የእጅ መታጠቢያ ሳሙና መኾኑን አብራርታለች፡፡
ለዚህ ሥራዋም አባቷ እገዛ እንደሚያደርጉላት ተናግራለች። ያመረተችውን ምርትም በአካባቢዋ መጠሪያ ገንደዳዩ ብላ በመሰየም ምርቱን በተለያዩ ባዛሮች በመሸጥ ከተጠቃሚዎች ጥሩ ምላሽ እንዳገኘች አንስታለች።
በቀጣይ የወረቀት ሳሙናውን በብዛት እና በጥራት በማሞረት ለገበያ ለማቅረብ ፍላጎት እንዳላት እና ጥረት እያደረገች መኾኑንም ገልጻለች።
#አሚኮ #innovations #Ethiopia
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
