ሀገር ችግር በገጠማት ጊዜ የውስጥ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው ለአንድነታቸው እየመከሩ ያሉት ኢትዮጵያውያን 🇪🇹

12

 

ኢትዮጵያውያን ተዋደው እና ተከባብረው በጋራ ጉዞ ሀገር እየገነቡ ዘመናትን ዘልቀዋል። የውስጥ ችግሮቻቸውን በሀገር በቀል የጥበብ መፍቻ መንገዶች እየፈቱ ኑረዋል።

በዚህም በበዳይ እና ተበዳይ መካከል የነበረውን ቂም አስወግደው አብረው መኖራቸውን ይቀጥላሉ። ኢትዮጵያውያን “ሰው ሰና ሰው ብቻ ሳይኾን እግር እና እግር እንኳ ይጋጫል” በሚለው ብሂላቸው ግጭት ያለ እና የሚኖር መኾኑን ተረድተው በተፈጠሩ አለመግባባቶች ሳይበገሩ ተስማምተው ይኖራሉ።

​”ልዩነት ውበት ነው፣ አንድነት ኀይል ነው” እንዲሉ፣ ሀገር ችግር በገጠማት ጊዜ የውስጥ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው በአንድነት በመቆም የውጭ ጠላትን ይመክታሉ። ሀገሪቱም በአብሮነት ጥበብ ታሪኳን አንጻ ታፍራ እና ተከብራ ኑራለች። ታሪኳም በዓለም አደባባይ የነገሰ፣ የማይጠፋ እና የማይደበዝዝ ህያው አሻራ ነው።

​አሁንም እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ሀገርን ለማስቀጠል እና ለነገው ትውልድ የጋራ ሀገር ለመገንባት ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው። በተለይም ዜጎች ስለጋራ እድላቸው እንዲያስቡ፣ የጋራ መፍትሄዎችን እንዲዘይዱ እና እርስ በእርሳቸው የበለጠ እንዲቀራረቡ ትልቅ ድርሻ አለው።

ይህ ሂደት ሕዝቦቿ “እናት ሀገር” ብለው ከመጥራት ባለፈ፣ በተግባር ለሀገር እንዲቆሙ የሚያስችል ጠንካራ መሠረት እንደሚጥል ይታመናል ።

በሠመራ ዩኒቨርሲቲ የሶሾዮሎጂ መምህር እና ተመራማሪ ኢፋ ታደሰ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ክስተት እና ከፍተኛ ትርጉም ያለው መኾኑን ይገልጻሉ።

ሂደቱ ከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል መጀመሩ የዜጎችን ባለቤትነት ለማረጋገጥ፣ ታሪካዊ ቅሬታዎችን እና ግጭቶችን በውይይት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፣ ባሕልን ለማዳበር፣ ማኅበረሰባዊ መተማመንን ለመገንባት እና የጋራ ኢትዮጵያን ለመመስረት ትልቅ መሰረት እንደኾነ ያስረዳሉ።

በተለይም ማኅበረሰቡን እና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት አንድ በማድረግ በኩል ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ የሚመለከታቸው መኾኑን አውቀው የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ይህም ለአንድነት ግንባታ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ያብራራሉ።

የተሠበሠቡ አጀንዳዎች እጅግ ውሥብሥብ የኾኑ እና ለዘመናት ያልተመለሱ ታሪካዊ ጥያቄዎች እና ቅሬታዎች በመኾናቸው አጀንዳዎች ላይ ሕዝቡ ተወያይቶባቸው መግባባት ላይ እንዲደርስ በማድረግ ለአንድነት ጠንካራ መሠረት ይጥላሉ።

ሀገራዊ ምክክሩ ከዚህ ቀደም ችግሮችን እና ልዩነቶችን በኀይል የመፍታት ልምድን የሚቀይር ነው። ይህም ችግሮቻችን በስምምነት፣ በድርድር እና በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ባሕልን ያዳብራል ነው ያሉት። የሰላም ግንባታ ባሕልን የቀየረ እና አንድነትን የሚያጠናክር መኾኑንም ነው የገለጹት።

በሀገሪቱ በተለያዩ ተቋማት አለመተማመኖች ነበሩ ያሉት መምህሩ ተቋማቱ ቅሬታቸውን በግልጽ አውጥተው እንዲነጋገሩ እና ዕውነታን መሠረት አድርገው ይቅርታቸውን አስወግደው መተማመን እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል ይላሉ።

በዚሁ አጋጣሚ የነበሩ ችግሮችን እንዲፈቱ፤ የነበሩ ግንኙነቶችን እንዲፈትሹ እና መልካም ነገሮችን እንዲያስቀጥሉ ያግዛልም ነው ያሉት።

ምክክሩ ዕውነትን መሠረት በማድረግ እርስ በርስ መተማመን እና መተጋጋዝ እንዲኖር ያደርገል። በውጭ ሀገር ጭምር የሚገኙ ዜጎች ለሀገር እንዲቆሙ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

አንዱ የሀገሪቱ ክፍል ሌላውን በተሳሳተ መንገድ የሚረዳበትን መንገድ በማጥበብ እና የጋራ መግባባትን በመፍጠር አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ የሚከፍት መኾኑን ነው የገለጹት። ይህ ሂደት ኅብረብሔራዊ አንድነትን ይገነባልም ብለዋል።

በሀገሪቱ የሀሳብ ልዕልና እንዲንግሥ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል። ወደፊትም ልዩነት ሳይገድባቸው በአንድ ማዕድ በጋራ የሚመክሩበትን እና ታላቋን ኢትዮጵያ የሚገነቡበትን ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

ምክክሩ ወደ ፊት አብረን ማልማት የምንችልበትን፣ ዘላቂ ሰላም የምናሰፍንበትን እና ጠንካራ የጋራ ኢትዮጵያን የምንገነባበትን ትልቅ መሰረት የሚጥል እንደኾነም አስገንዝበዋል። ለውይይት፣ ለሰላም እና ለጋራ ዕድገት ትልቅ በር ከፋች መኾኑንም ዶክተር ኢፋ ገልጸዋል።

#አሚኮ #ሀገራዊምክክር #peace

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም

ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🇪🇹 ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ኀላፊነቱን የሚወስዱት እነማን ናቸው?
Next articleየወረቀት ሳሙናን ለገበያ ያቀረበችው ወጣት ኢክራም