🇪🇹 ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ኀላፊነቱን የሚወስዱት እነማን ናቸው?

14

 

ሀገራዊ ምክክር የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ስብራቶችን በመጠገን እና ሀገርን በጠንካራ መሠረት ላይ ለማጽናት የሚያስችል ወሳኝ ዕድል ነው። ኢትዮጵያም በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከግጭት አዙሪት የወጣች ሀገርን ለመገንባት እየመከረች ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ ኮሚሽኑ በሀገሪቱ 1 ሺህ 234 ወረዳዎችን በማሳተፍ የሕዝቡን ፍላጎት እና ስጋት ያካተቱ ስምንት ሀገራዊ አጀንዳዎች ለዋናው ጉባኤ ቀርበው እየተመከረባቸው ነው ብለዋል። ይህም የዘመናት ችግሮችን በመፍታት፣ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ጠንካራ መተማመንን በመፍጠር ቅቡልነት ያለው ሀገረ-መንግሥት ለመገንባት ትልቅ ተስፋ የተጣለበት እንደኾነም ገልጸዋል።

ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ የተሳካ እንዲኾን እና ዘላቂ ሰላምን እንዲያመጣ የጥቂት አካላት ብቻ ሳይኾን የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ቅን ልቦና እና የማያወላውል ቁርጠኝነት እንደሚፈልግ በምክክር ሀገራቸውን ያሻገሩ ሀገራት ተሞክሮ ያሳያል።

በዋናነት:-

👉 የመንግሥት እና የገዥው ፓርቲ ቁርጠኝነት ከምንም በላይ ወሳኝ ነው። መንግሥት እንደመንግሥትነቱ ሂደቱን በመደገፍ፣ የሁሉንም ወገን ደኅንነት በማረጋገጥ እና ከምክክሩ የሚወጡ ውጤቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እውነተኛ የፖለቲካ ፍላጎት ሊኖረው እንደሚገባ ይመከራል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢትዮጵያን የኃይል ፖለቲካ አዙሪት በውይይት በመስበር፤ ለትውልድ የሚሻገር፤ ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ እና ለአፍሪካ አርዓያ የሚኾን ታሪካዊ የምክክር ውጤት እንዲመዘገብ በንቃት እና በድፍረት መምከር እንደሚገባ ማረጋገጣቸው ለዚህ ማሳያ ይኾናል።

👉 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ኃይሎች እና የፖለቲካ ልሂቃን ጠባብ የቡድን ፍላጎታቸውን ወደጎን በመተው ለሀገር ህልውና መቆም እንደሚኖርባቸውም ይታመናል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው ከኾነም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ እና የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎች በምክክሩ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

👉 የሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የምሁራን ሚና እጅግ የጎላ መኾን ይኖርበታል። እነዚህ አካላት ሕዝቡ በሂደቱ ላይ እምነት እንዲያሳድር በማድረግ፣ የፖለቲካ ልሂቃን ወደ ጽንፍ ሲያመሩ በማስታረቅ እና የሕዝቡን እውነተኛ ድምጽ በማስተጋባት በኩል ግንባር ቀደም ኀላፊነት ይጠበቅባቸዋል።

👉 መላው የሀገሪቱ ዜጎች በተለይም ወጣቶች፣ ሴቶች እና የተገለሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ በምክክሩ በንቃት በመሳተፍ እና የሀሰት መረጃዎችን በንቃት በመከላከል ለስኬቱ ዘብ መቆምም ይገባቸዋል።

👉 መገናኛ ብዙኃንም ሂደቱን በማያዳላ እና ሚዛናዊ በኾነ መንገድ በመዘገብ ገንቢ ሚናቸውን እንዲወጡም ይፈለጋል።

👉 የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ጣልቃ ገብነት በሌለው መልኩ የቴክኒክ እና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ለሂደቱ ስምረት የራሱን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። እነዚህ ሁሉ አካላት በጋራ ቆመው ስኬት ያመጡባቸውን የሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎች መመልከት ትልቅ ትምህርት ይሰጣል።

ለአብነትም፦

👉 በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓትን ለማስወገድ በተደረገው የኮዴሳ (CODESA) ድርድር ወቅት የፖለቲካ መሪዎቹ ኔልሰን ማንዴላ እና ኤፍ ደብሊው ዲክለርክ ያሳዩት ከፍ ያለ ቁርጠኝነት ሀገሪቱን ከከፋ የእርስ በርስ ደም መፋሰስ ታድጓታል። መሪዎቹ በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ሊደርስባቸው የሚችለውን ተቃውሞ በጸጋ ተቀብለው ለሀገር ሰላም ሲሉ ያደረጉት መቻቻል ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲኾን አስችሏል።

👉 የቱኒዚያ ተሞክሮም የሲቪክ ማኅበራትን ቁርጠኝነት በጉልህ ያሳየ ነው። በ2011 በተከሰተው የዐረብ ጸደይ አብዮት ማግስት ሀገሪቱ በከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ገብታ የእርስ በእርስ ጦርነት አፋፍ ላይ ደርሳ ነበር። በዚህ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነት ላይ መድረስ ሲያቅታቸው የሠራተኛ ማኅበራትን፣ የንግድ ምክር ቤትን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን እና የሕግ ባለሙያዎችን ያቀፈው “የቱኒዚያ ብሔራዊ የምክክር ኳርት” በወሰደው ቆራጥ አቋም የፖለቲካ ኃይሎቹ ወደ ጠረንጴዛ እንዲመጡ እና ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አስገድዷል። ይህ የሲቪክ ማኅበራቱ ቁርጠኝነት ሀገሪቱን ከጥፋት ከመታደጉም በላይ እ.አ.አ በ2015 የኖቤል የሰላም ሽልማት እንዲቀዳጁ አድርጓቸዋል።

በአጠቃላይ ሀገርን በምክክር የማጽናት ጉዞ የአንድ ተቋም ወይም የመንግሥት ኀላፊነት ብቻ ሊኾን እንደማይገባ በሂደቱ ያለፉ ሀገራት ተሞክሮ ያሳያል። ከደቡብ አፍሪካ እና ከቱኒዚያ ተሞክሮ እንደምንረዳው እውነተኛ ሀገራዊ መግባባት ሊመጣ የሚችለው የፖለቲካ መሪዎች ከልብ የመነጨ ፍላጎት ሲያሳዩ፤ የሲቪክ ማኅበራት እና የሃይማኖት አባቶች የሞራል የበላይነታቸውን ተጠቅመው መሐል ላይ ሲቆሙ፤ መላው ሕዝብ ለሰላሙ ቅድሚያ ሰጥቶ ሲንቀሳቀስ ብቻ ነው።

ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን ኀላፊነት በአግባቡ ከተወጡ ሀገራዊ ምክክሩ የነገዋን ብሩህ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል አስተማማኝ መሠረት ይኾናል።

#አሚኮ_ዜና #NationalDialogue #ኢትዮጵያ
#ባሕር_ዳር_ሐምሌ_14_2018ዓ_ም

በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ሠራዊቱ ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎን በበጎ አድራጎት ሥራዎች መሳተፉ ለሕዝብ እና ለሀገር የቆመ ዋልታ ስለመኾኑ የሚያስመሰክር ተግባር ነው” የሰከላ ወረዳ አሥተዳደር