
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ ዕዝ ዞብል ክፍለ ጦር የሠራዊቱ መሪዎች እና አባላት ከሰከላ ወረዳ አሥተዳደር ጋር “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት የችግኝ ተከላ እና የበጎ አድራጎት ሥራዎችን አከናውነዋል።
የዞብል ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ጀማል አማን እንደገለጹት የችግኝ ተከላዉ የተከናወነው ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን እውን ከማድረግ አኳያ ሠራዊቱም ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን እየተወጣ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ አስገንዝበዋል።
በዕለቱ የሠራዊት አባላት ከኪሳቸዉ ቀንሰዉ በማዋጣት ለአንዲት አቅመ ደካማ እናት የ22 ሺህ160 ብር ድጋፍ አድርገዋል። ቀጣይም ይህን መሰል የበጎ አድራጎት ተግባራት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አዛዡ ጠቁመዋል።
በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የተገኙት የሰከላ ወረዳ አሥተዳዳሪ ዓለማየሁ አዳነ ችግኝ መትከል የአፈር ለምነትን እና የአየር ንብረትን ከመጠበቅ ባሻገር ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሬዎችን በማልማት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሚያከናውነው የሰላም ማስከበር ተግባር ጎን ለጎን እየተሳተፈበት የሚገኘው የልማት እና የበጎ አድራጎት ተግባር እጅግ የሚያስመሰግነው እና ለሕዝብ እና ለሀገር የቆመ ዋልታ ስለመኾኑ የሚያስመሰክር ተግባር ነው ሲሉም አብራርተዋል።
የገንዘብ ድጋፍ የተደረገላቸው እናት በበኩላቸው የሠራዊቱ ድጋፍ የመጀመሪያ አለመሆኑን አውስተው ዛሬም ስለተበረከተላቸው ገንዘብ ምርቃት እና ምስጋና አቅርበዋል።
በችግኝ ተከላ የተሳተፉ የሠራዊት አባላት በሰጡት አስተያየት ተግባሩን ከዚህ በፊትም ሲያከናውኑት እንደነበር እና በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ዘገባው የምሥራቅ ዕዝ ነው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
