ችግኞችን ከመትከል ባሻገር ለጽድቀት በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው።

13
የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕንጻ አሥተዳደር እና አጠቃቀም ማዕከል በክልሉ ምክር ቤት ግቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውኗል። በተከላውም የቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ አማካሪዎች፣ የክልሉ የምርምር ኢንስቲትዩት እና በሥሩ የሚገኙ ተቋማት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
የማዕከሉ ሥራ አሥኪያጅ ዓለምነህ ይታየው እንደገለጹት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ በግቢው ውስጥ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ እና ተገቢውን የእንክብካቤ ሥራ ለመሥራት በሚያስችል መልኩ እየተተገበረ ይገኛል። ባለፈው ዓመት እንደ ቡና እና ፓፓያ ያሉ የኢኮኖሚ አቅም የሚፈጥሩ ችግኞች መተከላቸውን አስታውቀዋል። የጽድቀት ምጣኔውም ከ80 በመቶ በላይ መኾኑን ነው ያብራሩት።
በዘንድሮው ዓመትም ይህንኑ ስኬታማ ተሞክሮ በማስፋት አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ሙዝና ቡና በክላስተር እየተተከለ እንደኾነ አስታውቀዋል። ይህ አሠራር ለምርት አሠባሠብ፣ ለክትትል እና ለማኔጅመንት ሥራዎች ምቹ እንዲኾን ታስቦ የተተገበረ ነው።
ግቢውን ይበልጥ አምራች ለማድረግ ማዕከሉ ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ፣ ከክልሉ ምርምር ኢንስቲትዩት እና በስሩ ከሚገኙ ተቋማት ጋር በጋራ እየሠራ መኾኑን አስታውቀዋል።
አሁን ላይ በግቢው የተተከሉ ችግኞች እና አትክልቶች ለማዕከሉ ተጨማሪ የገቢ አቅም እየፈጠሩ መኾኑንም ጠቁመዋል። ለአብነትም በግቢው የለሙት እንደ አይደርቄ ጎመን፣ ቆስጣ እና ስኳር ድንች ያሉ አትክልቶች ለማዕከሉ ገቢ እያስገኙ መኾኑ ነው የተብራራው።
በግቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ለምርምር ተቋማት ተጨማሪ አቅም ከመኾናቸውም ባሻገር የምክር ቤት አባላት የተሻለ ተሞክሮ በመውሰድ አሠራሩን በሁሉም አካባቢዎች እንዲያስፋፉ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በግቢው የሚተከሉ ችግኞች ጸድቀው የማዕከሉን ገቢ በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው ለማድረግ የሆርቲካልቸር ባለሙያዎች መመደባቸውን ጠቁመዋል።
ለቋሚ አትክልተኞች ተገቢው ሥልጠና እና ድጋፍ እየተደረገ መኾኑ ለችግኞቹ የጽድቀት ምጣኔ መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ተመላክቷል።
በተከላው የተሳተፉ ሠራተኞች እና መሪዎችም የአረንጓዴ አሻራ የአካባቢ ሥነ ምህዳርን በመመለስ እና ምርታማነትን በማረጋገጥ ጉልህ ሚና እያበረከቱ መኾኑንም ተናግረዋል።
#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 14/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleመደማመጥ የችግሮች መፍቻ ቁልፍ
Next article“ሠራዊቱ ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎን በበጎ አድራጎት ሥራዎች መሳተፉ ለሕዝብ እና ለሀገር የቆመ ዋልታ ስለመኾኑ የሚያስመሰክር ተግባር ነው” የሰከላ ወረዳ አሥተዳደር