
ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ በማኅበራዊ መስተጋብር እና በትውፊት የታነጸ የጋራ እሴት ያላት ሀገር ናት።
ከእሴቶች መካከልም መደማመጥ እና መመካከር ለሀገር ሰላም እና ለአብሮነት ዋነኛ ምሰሶ ኾነው ዘመናትን አገልግለዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ የመደማመጥ ባሕል እየተሸረሸረ መምጣቱ እና በምትኩ አለመግባባት፣ የሃሳብ መገፋፋት እና አለመቻቻል እየነገሡ መጥተዋል። ይህም ለዘርፈ ብዙ ችግሮች እየዳረገ ይገኛል።
በቀደመው ሥርዓት እና ትውፊት ኢትዮጵያውያን ለሽምግልና፣ ለዕርቅ እና ለምክር ትልቅ ቦታ ይሰጡ ነበር። አባቶች በትልልቅ ዛፍ ስር ወይም በተመረጠ ቦታ ተቀምጠው የቱንም ያህል የከረረ ቂም ቢኖር በንግግር እና በብልሃት ይፈቱትም ነበር።
ደራሲ ዮናስ አድማሱ (ዶ.ር) በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር መጽሔት ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ የባሕል መናጋቱን ሲያስረዱ የዘመናችን ትልቅ ቀውስ “እኔ ብቻ ልናገር፣ እኔ ብቻ ልወቅ” ባይነት ነው ብለው ነበር። መደማመጥ በሌለበት ማኅበረሰብ ውስጥ ደግሞ አብሮነት አይኖርም ነው ያሉት።
ይህም አሁን ላይ እየተስተዋለ ላለው ያለመደማመጥ ሁኔታዎች አንዱ ማሳያ ነው። የመደማመጥ ባሕል እየጠፋ በመምጣቱም እርስ በእርስ መጠራጠር እየገነነ መተማመን እየጠፋ መጥቷል።
ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በሰላማዊ ውይይት የመፍታት አቅም እያሳጣም ነው። ይህም የጋራ ታሪክን ወደ ጎን በመተው ሀገራዊ አንድነትን ጥያቄ ውስጥ እያስገባው መጥቷል።
በቀደመው ዘመን የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ፈጣሪን ፍሩ፤ ታረቁ ሲሉ የጦር መሣሪያ የያዘ ኀይል እንኳ መሣሪያውን ያወርድ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የእነሱም ተደማጭነት እየቀነሰ እና ለፖለቲካዊ ጥቅሞች ተጋላጭ የመኾን አዝማሚያ ይስተዋላሉ።
ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን ሀገር ሽማግሌ ስታጣ፣ ወጣት ምክር ሲንቅ፣ ያኔ ሀገር ይናጋል ነበር ያሉት። አሁን ላይ እየኾነ ያለውም ይሄው ነው። ሽማግሌዎች የሀገር የሰላም ሚዛኖች ነበሩ። ናቸውም።
ታዋቂው የመብት ተሟጋች እና ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “መክሸፍ እንደ …. ታሪክ”በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ሽማግሌዎችን እና የሃይማኖት አባቶችን ማክበር ያቆመ ትውልድ የራሱን ታሪክ እና መጻኢ ዕድል እያጠፋ ነው፤ ዕውቀት በዕድሜ እና በልምድ ይገነባል፤ እኛ ግን የሽማግሌዎቻችንን ቃል ማቃለል ጀምረናል በማለት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የትውልዱን አለመደማመጥ አመላክተዋል።
የሃይማኖት አባቶች እና በዕድሜ ገፋ ያሉ አባቶችም ሚናቸውን መልሰው እንዲያገኙ ወጣቱ ትውልድ ደግሞ በትሕትና የመስማትን ጥበብ ሊለማመድ ይገባል።
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_14_2018 ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
