4ሺህ ድምጾች በኢትዮጵያ የንጋት ወጋገን ላይ…

14
👥 የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ለረጅም ዘመናት “እኔ ብቻ ልክ ነኝ” በሚል የዜሮ ድምር ፖለቲካ እና በታጣቂዎች የሥልጣን ሽኩቻ ሢመራ የቆዬ ነበር ማለት ይቻላል። ይህ የቆዬ አደገኛ ባሕል ሀገሪቱን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏታል።⚠️
አሁን ግን ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው በማታውቀው መልኩ ሰፊ የሕዝብ ስብጥርን ያቀፈ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ እያካሄደች ትገኛለች። ይህ መድረክ የቆየውን ጎጂ አካሄድ በመስበር ለአዲስ የፖለቲካ ባሕል መሠረት እየጣለ ነው።
✍️ የሃሳብ የበላይነትን በውይይት የመትከል ጉዞ ! የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የምክክሩን ዋና ዓላማ ሲያስረዱ የሀገራዊ ምክክር ግቡ የፖለቲካ ልዩነቶቻችን በሳይንሳዊ፣ በሠለጠነ እና እርስ በእርስ በመደማመጥ ለመፍታት የሚያስችል ባሕል መገንባት እንደኾነ መግለጻቸው ይታወሳል።
ይህም የሀሳብ የበላይነትን በመሳሪያ የመጫን ባሕልን እንደሚያስቀር ገልጸዋል። በምትኩ ልዩነቶችን በሀሳብ እና በምክክር የመስማማት የፖለቲካ ባሕልን የሚተክል መኾኑንም ነው ያስረዱት።
👉 ከሊህቃን የበላይነት ወደ ሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎ ! ይህ ምክክር ከፖለቲካ ልሂቃን አልፎ ከአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች እስከ ምሁራን፣ ከሴቶች እና ወጣቶች እስከ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ያካተተ፣ ሁሉንም ብሔሮች ያቀፈ ነው። ሂደቱ ከፖለቲካ ሊህቃን ወይም ከታጣቂ ቡድኖች ጋር ብቻ ከመደራደር ይልቅ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እኩል ሚዛን እንዲኖረው አድርጓል።
👴♿
በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም የምክክሩ ትልቁ ስኬት የሚለካው በሚወጡት ሰነዶች ብቻ ሳይኾን ሕዝቡ እርስ በእርሱ እንዲነጋገር እና የሌላውን ወገን እይታ እንዲረዳ በመደረጉ ነው ብለዋል።
🕊️ እንደ ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ የምክክር ሂደቱ የታሪክ ስብራቶችን እና መዋቅራዊ በደሎችን በግልጽ በመወያየት መፍትሔ ለመፈለግ የተዘጋጀ ታሪካዊ ዕድል ነው።
ምክክሩ የተለመደውን የሊህቃንን የበላይነት በማስወገድ በቀጥታ ወደ ሕዝብ ተሳትፎ ያመራ ዘመናዊ የግጭት አፈታት መንገድ መኾኑን አብራርተዋል።
በዚህ የታሪካዊ ጉባኤ አካል ለመኾን በመቻላቸው ትልቅ ክብር እና ኩራት እንደተሰማቸውም ገልጸዋል።
“ላለፉት 40 እና 50 ዓመታት በጠበቃነት፣ በማስተማር፣ በጋዜጠኝነት እና በተሟጋችነት ያሳለፍኩት ሕይወት ‘እኔ ካላሸነፍኩ’ የሚል የዜሮ ድምር ፖለቲካ ነበር” የሚሉት ፕሮፌሰሩ “አሁን ግን የሁሉንም አሸናፊነት በሚያረጋግጠው የ4 ሺህ አባላቱ የምክክር ጉባኤ ቡድን አካል በመኾን ትልቅ ዕድል አግኝቻለሁ” ብለዋል።
✍️ የተስፋው ንጋት 🌅✨
በዓይነቱ ልዩ የኾነው ይህ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያን ለዘመናት አስረው ከያዟት የታሪክ እና የፖለቲካ ውዝግቦች አውጥቶ ወደ አዲስ የሰላም እና የልማት ምዕራፍ የሚያሸጋግር “የንጋት ወጋገን” ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
በመድረኩ የሚደመጡት 4 ሺህ ድምጾችም የብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ምኞት፣ ተስፋ እና ስጋት ይዘው በመቅረብ ሀገሪቱን ከግጭት ፖለቲካ ወደ ውይይት እና ይቅር ባይነት የሚያሸጋግር ጠንካራ መሠረት እንደሚጥል ተስፋ ተጥሎበታል።
✍️ በአሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሆርቲ ካልቸር ምርቶችን ጥራት በማረጋገጥ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ እየተሠራ ነው።
Next articleመደማመጥ የችግሮች መፍቻ ቁልፍ