
የሆርቲ ካልቸር ዕውቅና አሰጣጥ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው። ጠንካራ የግብርና ማረጋገጫ ሥርዓት መኖሩ የኢትዮጵያን የሆርቲ ካልቸር ምርቶች ጥራት በማረጋገጥ በዓለም ገበያ ያላቸውን ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድግ የኢትዮጵያ የሆርቲ ካልቸር አምራቾች እና ላኪዎች ማኅበር አስታውቋል።
የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ዘውዴ የማረጋገጫ ሥርዓቱ የምርቶችን ጥራት እና ደኅንነት ከማረጋገጥ ባሻገር የውጭ ገበያ ተደራሽነትን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለመጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።
ማኅበሩም ከመንግሥት ተቋማት፣ ከግሉ ዘርፍ እና ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር አምራቾች እና ላኪዎች ዓለም አቀፍ የጥራት መሥፈርቶችን እንዲያሟሉ የአቅም ግንባታ፣ የሥልጠና እና የቴክኒክ ድጋፍ ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑንም ገልጸዋል።
የግብርና ማረጋገጫ ሥርዓትን በማጠናከር የኢትዮጵያ ሆርቲ ካልቸር ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ያላቸውን ቦታ ማስፋት እና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚቻልም ነው የተናገሩት።
ጠንካራ የግብርና ማረጋገጫ ሥርዓትን መገንባት የኢትዮጵያን የግብርና ምርቶች ጥራት እና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ወሳኝ መኾኑም ተጠቁሟል።
በዚህም የአምራቾች እና የላኪዎችን አቅም ማሳደግ፣ ዓለም አቀፍ የጥራት መስፈርቶችን ማሟላት እና የውጭ ገበያ ተደራሽነትን ማስፋት ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ እና የግብርናውን ዘርፍ በዘላቂነት ለማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ አየለ መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
