“የዱር እንሰሳት እና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ የአንድ ተቋም ብቻ ሳይኾን የጋራ ሥራ ነው” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

10
የኢትዮጵያ የዱር እንሰሳት ባለሥልጣን የተመሠረተበትን 60ኛ ዓመት የኢዮቤልዮ ማጠናቀቂያ በዓል በዓድዋ ሙዚየም አክብሯል።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ባለፉት 60 ዓመታት በጥበቃ ቦታዎች እና በዱር እንስሳት መኖሪያ አካባቢዎች የሚከሰቱ የሰው እና የዱር እንስሳት ግጭቶችን በመጠበቅ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ ብሔራዊ ፓርኮችን ከሰው ሠራሽ ችግሮች ለመታደግ የተቀናጁ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል ብለዋል።
በተለይም ለሕገወጥ አደን፣ ለእሳት አደጋ እና ለልቅ ግጦሽ የተጋለጡ ተራራዎች እና ብሔራዊ ፓርኮች ችግሮችን ከመሠረቱ ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በዱር እንስሳት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ውሥብሥብ እየኾኑ በመምጣታቸው ከወንጀል ፈጻሚዎች ቀድሞ ለመድረስ የብዝኀ ሕይወት ጥበቃ ባሕልን ማጠናከር፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም እና የባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ አስፈላጊ መኾኑን አንስተዋል።
የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስትር ድኤታ እንደገና አበበ (ዶ.ር) ባለፉት 60 ዓመታት ብሔራዊ ፓርኮችን ከሰው ሠራሽ ችግሮች ለመታደግ የተቀናጁ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ለእሳት አደጋ እና ለሕገ-ወጥ አደን የተጋለጡ ፓርኮች መጠበቃቸው ችግሮቹን ከመሠረቱ ለመፍታት የተሠሩ እና ተጨባጭ ውጤት የተመዘገበባቸው ናቸው ብለዋል።
በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ፀጋ የታደለች መኾኗን ጠቅሰዋል። የዱር እንስሳት ሀብት የሕዝብ ሀብት በመኾኑ ሁሉም ይህንን ሀብት የመጠበቅ ሀገራዊ ኀላፊነት አለበት ብለዋል።
የዱር እንሰሳትን መጠበቅ የአንድ ተቋም ብቻ አይደለም፣ የጋራ ሥራችን ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የምርጫ ሳይኾን የሕልውና ጉዳይ በመኾኑ የዱር እንስሳት ጥበቃን በማጠናከር ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ማሳደግ ይቻላል ነው ያሉት።
በተለይም በብዝኀ ሕይወት ሀብት የታደለችውን ሀገራችንን ከፍ ማድረግ እና ለዱር እንስሳት ጥበቃ ሥራም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል ብለዋል።
#አዲስ_አበባ፡ ሐምሌ14/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleለቀጣዩ ትውልድ የአየር ንብረቷ የተጠበቀ እና የለመለመች ኢትዮጵያን ለማውረስ አረንጓዴ አሻራ ወሳኝ ነው
Next articleየሆርቲ ካልቸር ምርቶችን ጥራት በማረጋገጥ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ እየተሠራ ነው።