
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች እና ሠራተኞች“ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ መልዕክት በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር በዘንዘልማ ቀበሌ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂደዋል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት የግብርና ሚኒስቴር አማካሪ ማርቆስ ሊራንጎ የክረምት አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እንደ ሀገር 8 ነጥብ 6ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ የተከላ መርሐ ግብሩ እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል።
ዛፍ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ቁርኝት አለው ያሉት አማካሪው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ ወዲህ እንደ ሀገር የመትከል ባሕል እያደገ መጥቷል ብለዋል። በክልሉ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በመሣተፋቸው ደስተኛ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። የክልሉ ሕዝብ የተተከሉ ችግኞች የልማት ባለቤት በመኾን መንከባከብ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኅላፊ ደረጀ ማንደፍሮ በክልሉ የ2018/19 የክረምት አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ መልዕክት በሁሉም አካባቢዎች በስፋት እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።
በዚህ ዓመት 1ነጥብ 76 ቢሊዮን የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ፋይዳ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተተከለ ይገኛል ነው ያሉት።
ለዚህም የሚኾን ከ264 ሺህ ሄክተር በላይ መሬት መዘጋጀቱን አንስተዋል። እስካሁን በተከናወኑ ሥራዎችም ከ442 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውንም ነው የገለጹት።
ባለፉት ሰባት ተከታታይ ዓመታት ከ10 ነጥብ 6ቢሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን አውስተዋል። በዚህም ከ 1ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሄክታር የተራቆተ መሬት በአረንጓዴ አሻራ ማልበስ ተችሏል።
የክልሉ የደን ሽፋን ከነበረበት 14 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 18 ነጥብ 9 በመቶ ከፍ ማለት ችሏል ነው ያሉት። የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ምርታማነትን ማሳደግ እና የከርሰ ምድር ውኃ በማጎልበት የነበረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በተለይም በተፋሰስ በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ወጣቶች በከብት ማድለብ፣ በንብ ሀብት ልማት እና በሌሎችም ዘርፎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
ዘንድሮም በተለይም በፍራፍሬ ልማት እንደ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓዬ፣ ማጎ እና ቡና በኩታገጠም ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል። በዚህም ማኅበረሰቡን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ ይሠራል።
ይህ የአረንጓዴ አሻራ ሥራ የነገውን ትውልድ ደኅንነት የማረጋገጥ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም እና የካርቦን ልቀትን ለመከላከል ትልቅ አቅም ነው ብለዋል።
ችግኝ በመትከል አሻራ ማስቀመጥ እና የተተከሉ ችግኞች በዘላቂነት እንዲጸድቁ በባለቤትነት መንከባከብ የሁሉም ኀላፊነት መኾኑን አስገንዝበዋል።
በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የዘንዘልማ ቀበሌ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አበባ ኅይሉ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ለፍሬ እንደሚያበቁ ገልጸዋል። በዚህ ክረምት በቀበሌው ከ8ሺህ በላይ ችግኞች እንደሚተከሉም ገልጸዋል።
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_14_2018 ዓ_ም
በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
