ጠመንጃ ያፈረሰውን

11
🤝 ጠረጴዛ ይገነባዋል!
ሀገራት የውስጥ ችግር ሲያጋጥማቸው ፈተናዎችን ለማለፍ በአንድነት ተሠባሥበው ይመካከራሉ። ሀገራዊ ምክክርን በማድረግም በርካታ ሀገራት ሀገራቸውን ከጥፋት መታደግ ችለዋል።
🤝የደቡብ አፍሪካ ተሞክሮ:- በቀልን በይቅርታ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ በከፋ ችግር ውስጥ የነበረችው ደቡብ አፍሪካ ዜጎቿ በባለብዙ ወገን ውይይት የፖለቲካ ኀይሎችን በጠረጴዛ ዙሪያ በማሠባሠብ ሀገሪቱን ከእልቂት መታደግ ችለዋል።
ምክክሩ የሀገር ባለቤትነት ስሜትን አጠናክሮላቸዋል፤ ለዘላቂ ሰላም መሠረት ጥሏል። በቀልን በይቅርታ በመተካት፣ ተጎጂዎች ድምጽ እንዲያገኙ እና በዳዮች ምኅረት እንዲጠይቁ በማድረግ በሀገሪቱ የጋራ መግባባትን መፍጠራቸውን ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ በወቅቱ ይዞት የወጣው መረጃ ያትታል።
🤝 የኮሎቢያ ጉዞ:-የ50 ዓመታት የግጭት ፍጻሜ ሌላው በኮሎምቢያ መንግሥት እና በፋርክ አማጽያን መካከል በሀገሪቱ ለ50 ዓመታት የዘለቀውን እና የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈውን ግጭት ማስቆም የተቻለው በሀገራዊ ምክክር በተደረሰ ስምምነት ነው።
የኮሎምቢያ ሀገራዊ ምክክር በዓለም ላይ እጅግ ውሥብሥብ እና ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ ግጭትን በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት ረገድ በምሳሌነት የሚጠቀስ ታሪካዊ ክስተት ነው። በ2012 በፕሬዝዳንት ሁዋን ማኑኤል ሳንቶስ የሚመራው መንግሥት “የሃቫና ውይይት” የተሰኘ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ምክክር አድርጓል። በዚህም በሀገሪቱ ሁሉም ዜጎች ተወክለው ተሳታፊ ኾነዋል።
የጉባኤው ውጤትም የመሬት ፖሊሲ እንዲሻሻል፣ የፖለቲካ ተሳትፎ ማስፋት፣ ከመንግሥት ውጭ ያሉ ታጣቂዎች ትጥቅ እንዲፈቱ፣ የዕፅ ዝውውርን በጋራ መዋጋት እና ለጦርነቱ ሰለባዎች ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ አሥችሏል። የሀገራቸውን አንድነት አስጠብቀው እንዲዘልቁም ማስቻሉን በወቅቱ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ይዞት የወጣው መረጃ ያሳያል።
🤝የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር፦ የዘመናት ቁስል ፈውስ”
🇪🇹ኢትዮጵያም የውስጥ ችግሮቿን በውይይት ለመፍታት የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ እያካሄደች ነው። በጉባኤው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ድምጻቸውን ያሰሙበት፤ ለሀገራዊ መጻኢ ዕድል በጋራ ለመወሰን የተቀመጡበት ኾኗል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአማካሪ ኮሚቴ አባል ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ የምክክር ኮሚሽኑ ሂደት የኢትዮጵያ የዘመናት ችግሮችን የሚፈታ ነው ብለዋል። አጀንዳዎቹ የሀገሪቱን ችግር ለቅመው የያዙ በመኾኑ ለኢትዮጵያ መድኀኒት ነውም ብለዋል።
የችግሩ ገፈት ቀማሽ፤ የችግሩ የመፍትሔ አካል ራሱ ሕዝብ በመኾኑ ሕዝቡ በባለቤትነት እየተወያየ ነው ብለዋል። ውይይቱ ስኬታማ ውጤትን ያስመዘግባልም ነው ያሉት።
ጉባኤው የጋራ መግባባትን የሚፈጥር፤ የኢትዮጵያ ሕዝብን በአንድነት የሚያስተሳሰር፤ ለወደፊት ችግሮች ሲፈጠሩ ውይይትን እንድናስቀድም የሚያስችል፤ ችግሮችን በውይይት የሚፈቱ ተቋማት እንዲፈጠሩ የሚያደርግ፤ የምክክር ባሕል እንዲዳብር የሚያስችል አዲስ ተግባርን ለኢትዮጵያ ያመጣል ብለዋል።
ውጤት የሚያስገኝ ሰላማዊ ትግል መኾኑን ገልጸዋል። ሰላማዊ ትግል ማለት ለአንድ መፍትሔ ሕዝብን ማታገል ነውም ብለዋል። ጠመንጃ ወጣቶች ሕይወትን ሳያጣጥሙ እንዲቀጠፉ ከማድረግ ውጭ የሚያስገኘው ጠቀሜታ የለም ብለዋል።
በመኾኑም ውይይት እና ምክክርን በማስቀደም የግጭት አማራጭን በመተው ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዋን ልጅ አቅፋ ያስፈተነችው የፌዴራል ፖሊስ አባል
Next articleለቀጣዩ ትውልድ የአየር ንብረቷ የተጠበቀ እና የለመለመች ኢትዮጵያን ለማውረስ አረንጓዴ አሻራ ወሳኝ ነው