የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዋን ልጅ አቅፋ ያስፈተነችው የፌዴራል ፖሊስ አባል

23
‎​በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና እየተሰጠ ባለበት ወቅት አንዲት ተፈታኝ እናት አራስ ልጇን የሚይዝላት ሰው በማጣቷ ልጇን አቅፋ ወደ መፈተኛ ማዕከል መግባት ግድ ይኾንባታል።
እናቲቱ ሕፃኗን ይዛ ፈተናውን ለመፈተን ባደረገችው ጥረት፣ የሕጻኑ ለቅሶ እና መነጫነጭ ለዓመታት የለፋችበትን እና የወደፊት ሕይወቷን የሚወስነውን ፈተና በትኩረት ለመሥራት ፈተና ኾነባት።
‎​ይህን ድርጊት የተመለከትችው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አባል ረዳት ሳጅን ራቢያ አብደላ ከተመደበችበት የጸጥታ ማስከበር ሥራ ጎን ለጎን ሕፃኗን ከእናቷ በመቀበል በእቅፏ አቆየች።
‎”ፖሊስነት እናትነት እና ርህራሄ ነው” የምትለው ረዳት ሳጅን ራቢያ፣ የእናቲቱ የወደፊት ሕይወት ሊቀይር የሚችለውን የፈተና እድል በዚህ እንዳይሰናከል፣ እናቲቱ ፈተናዋን ሙሉ በሙሉ አጠናቅቃ እስክትወጣ ድረስ ልጇን በከፍተኛ እንክብካቤ ይዛ በመቆየት፣ ተፈታኟ በሙሉ ልቧ ተረጋግታ ፈተናዋን እንድትፈተን ማድረጓን ገልጻለች።
‎​የሕጻኗ እናትም “እህቴ ክብር ይገባሻል፤ ፖሊስ ሕግን ማስከበር ብቻ ሳይኾን ሰውን በክብር እና በርህራሄ ማገልገል መኾኑን በተግባር አሳይተሻል፤ መልካም ሰው መኾን ትልቅ ማዕረግ ነው፤ የአንቺን አርአያ ሌሎች ይከተሉ ” ብላለች። ላደረገችላት እንክብካቤ እና እገዛም ምስጋና አቅርባለች።
‎​የረዳት ሳጅን ራቢያ አብደላ ይህ ሰብዓዊነት የታከለበት ተግባር፣ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብን እና ነዋሪዎችን ቀልብ የሳበ ኾኗል። የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አባላትም የፖሊስ አባሏ የፈጸመችው ይህ ተግባር ማንኛውም ዜጋ በተሰማራበት የሥራ መስክ መልካምነትን እና ሰብዓዊነትን እንዲተገብር ትልቅ ማሳያ መኾኑን ገልጸዋል።
‎​አንድ የመልካም ተምሳሌት ተግባር ለሌሎች አርአያ እንዲኾን ማበረታታት ከሁሉም አካላት እንደሚጠበቅም ተመላክቷል።
ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የረዳት ሳጅን ራቢያ ድርጊት የፖሊስ አባላት ለሰው ልጅ ያላቸውን ክብር እና የሰብዓዊነት ስሜት ያሳየ ነው።
‎በጀግንነት መጠበቅ፤ በሰብዓዊነት ማገልገል ማለት ይህ ነው። በጀግንነት መጠበቅ፣ በሰብዓዊነት ማገልገል በተግባር ሲገለጥም እንደዚህ መኾኑን የፌዴራል ፖሊስ ገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሳይበር ጥቃትን እንዴት መከላከል ይቻላል?
Next articleጠመንጃ ያፈረሰውን