
ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን በ2013 ዓ.ም በከፈተው ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ በደል ፈጽሟል። በዚያ ጦርነት ብዙዎች ሞተዋል፤ ከፍተኛ ሀብትም ወድሟል።
ሕገ ወጥ ቡድኑ የትግራይ ወጣቶችን በሀሰት ፕሮፖጋንዳ በማነሳሳት እና በማሳሳት ለጦርነት ማግዷል። ወጣቶችንም ለሞት እና ለአካል መጉደል ዳርጓል።
ሕገ ወጥ ቡድኑ የፈረመውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ጊዜ በመግዛት በኋላም ስምምነቱን በመጣስ ለሌላ ዙር ጦርነት ሰፊ ዝግጅት እያደረገ ነው። አሁንም በአሳዛኝ ሁኔታ የቀሩትን ወጣቶች ዋጋ ለማስከፈል አስገድዶ ወደ ጦር ማሠልጠኛ ማዕከል አፈሳ እያደረገ መኾኑን የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ነው።
የሕገ ወጥ ቡድኑን ሴራ እና ዓላማ የተገነዘበው የትግራይ ክልል ሕዝብም ከሕጻን እስከ አዋቂ ሕገ ወጥ ቡድኑን እየተቃወመ ይገኛል።
በሚያሰራጨው ፕሮፖጋንዳ እንደቀድሞው አይታለልም። ወጣቶች ከክልሉ እየወጡ ነው፤ ከክልሉ መውጣት ያልቻሉት ከአስገዳጅ አፈሳው ለማምለጥ የራሳቸውን ስልት ቀይሰው በኅብረት ራሳቸውን እየተከላከሉም ይገኛሉ። እናቶች ልጆቻችንን ለጦርነት አንሰጥም በማለት ሕገ ወጥ ቡድኑን ፊት ለፊት ሲቃወሙ ተስተውለዋል።
ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች፣ ቀንደኛ ደጋፊው የነበሩ የማኅበራዊ ሚዲያ ጸሐፊዎች፣ ዲያስፖራዎች እና አርቲስቶች ሳይቀሩ የቡድኑን ሴራ ተረድተው “የትግራይ ክልል ሕዝብ ሰላም ይፈልጋል፤ ጦርነት ይብቃ” በማለት የሕገ ወጥ ቡድኑን አስገዳጅ አፈሳ እና የጦርነት ዝግጅት እየተቃወሙ ታይተዋል።
በቅርቡ ደግሞ የትግራይ ተወላጅ የኾኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሕገ ወጡን ቡድን የሚያቃወም ሰላም ሰልፍ አካሂደዋል።
አምስት ልጆች እንዳሏቸው በመግለጽ የሕገ ወጥ ቡድኑን እንቅስቃሴ ያወገዙ አንዲት እናት “ልጆቼን ለጦርነት እንውሰድ ከሚሉኝ እኔን ቢወስዱኝ እመርጣለሁ” ብለዋል።
ይህን ማንኛዋም የትግራይ እናት የማትፈልገው እና የማትፈቅደው ነው፤ እንደ ትግራይ ክልል ተወላጅ ብቻም ሳይኾን እንደ ሰው ጦርነትን ማንም አይፈልግም” ነው ያሉት።
“እናቶች ካለፈው ሀዘን አላገገሙም፤ ያለፈው ሞት ይብቃን፤ የእናቶች እንባ እና ለቅሶ ይብቃ” በማለትም ሕገ ወጡን የሕወሃት ቡድን የሚፈጽመውን አፈሳ እና የሚያደርገውን የጦርነት ዝግጅት ኮንነዋል።
ሌላኛዋ እናትም ከጦርነት ኪሳራ እንጅ በፍጹም ትርፍ እንደማይገኝ ካለፉት ዓመታት አውዳሚ ጦርነት አይተነዋል ነው ያሉት። የሕገ ወጡ ሕወሃት የወጣቶች አፈሳ እና የጦርነት ዝግጅት ወጣትን የማጥፋት፤ ሀገርን የማፍረስ ክፉ ሥራ ነው በማለት ሕወሃት የትግራይ ሕዝብን ከማጥፋት ውጪ ሌላ ጥቅም እንደማይኖረው ገልጸዋል።
የሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን መሪዎች የትግራይ ሕዝብን ሀብት በመዝረፍ ልጆቻቸውን በውጭ ሀገር በምቾት እንደሚያኖሩ ተናግረዋል። ጦርነት ውስጥ እንዲገቡባቸውም አይፈልጉም ብለዋል። ነገር ግን በራሳቸው ላይ እንዲደረግ የማይፈልጉትን ነገር በትግራይ ድሃ እናቶች ላይ እያደረጉት ይገኛሉ ነው ያሉት።
በትግራይ ክልል ልጅ ወልደው ያሳደጉ እና ወጣት ልጆች ያሏቸው እናቶች በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ አሳውቀዋል። ስለኾነም የትግራይ ክልል እናቶች የሰቆቃ ኑሮ ሊያበቃ ይገባል ብለዋል። ትውልድ እያጠፉ የሚገኙ የሕገ ወጡ ሕወሃት አካላትን መንግሥት ሊያስቆማቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
