
በደቡብ ጎንደር ዞን የደራ ሀሙሲት ወረዳ መሪዎች እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት መሪዎች በቀጣናው የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት ለመገንባት የሚያስችል ውይይት አድርገዋል። የአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች እና የመሥተዳደር አካላት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በቅንጅት በመሥራታቸው አሁን የሚታየውን ሰላም እንዳስገኘ ተጠቁሟል። የዛሬው ውይይትም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የቅንጅት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው የተነሳበት ነበር።
የውይይት መድረኩን የመሩት የደራ ሃሙሲት ወረዳ አሥተዳዳሪ እውነቱ ተሻገር እንደተናገሩት በሠራዊቱ መስዋዕትነት የተገኘውን ሠላም ጠብቆ ለማስቀጠል የተከፈለውን መስዕዋትነት ማሰብ እና የታለፈበትን ሁኔታ ሁሌም ማስታወስ ይኖርብናል ብለዋል።
እንደ አሥተዳዳሪው ሠራዊቱ ሕዝብን ከራሱ አስቀድሞ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ጠላትን ፊት ለፊት ተጋፍጧል” ብለዋል። ይህንን ቁርጠኝነትም አድንቀዋል። የተገኘውን ሠላም ወደፊት ለማስቀጠል ጠንክረን እንሠራለን ነዉ ያሉት።
በጣናው የሚገኝ የምሥራቅ ዕዝ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ ለውጊያ ድጋፍ አገልግሎት ሌተናል ኮሎኔል መሐመድ እንድሪስ እንዳሉት የተመዘገቡ ድሎች በሕዝቡ ያልተቋረጠ ድጋፍ እና በፀጥታ ኃይሉ አብሮነት የተገኙ ናቸው። ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ የቅንጅት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የተገኙት የክፍለ ጦሩ ከፍተኛ መኮንኖች ሕዝቡ የሰላሙ ባለቤት ራሱ መሆኑን በማመን፣ ለሠራዊቱ መረጃ በማቀበል፣ የጠላትን የሎጀስቲክስ ምንጭ በማድረቅ እና አካባቢያቸውን ነቅተው በመጠበቅ ከሠራዊቱ ጋር የማይቋረጥ አንድነትን እንዲያስቀጥሉ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
ዘገባው የምሥራቅ ዕዝ ነው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
