
በሀረሪ ክልል በ2018 በጀት ዓመት የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሰላምን ለማጽናት በተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ሥራዎች መመዝገባቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አሕመድ አብዲ የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አደረጃጀቶች እና ሕዝቡን የሰላሙ ባለቤት አድርጎ ተከታታይ ሥልጠናዎችን በመስጠት የፖሊስ አጋርነታቸውን እንዲያጠናክሩ መደረጉን ገልጸዋል።
ይህም በክልሉ የወንጀል ተግባራት እንዲቀንሱ ከማስቻሉም በላይ የፖሊስ የሥራ ጫናን ማቃለሉን ነው የተናገሩት።
ኮሚሽኑ የሰው ኃይሉን በማሳደግ በሥነ ምግባር የታነጹ እና በዕውቀት የበለጸጉ የፖሊስ አባላት እንዲኖሩት ለማስቻል በትኩረት መሠራቱን ገልጸዋል።
በክልሉ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሰላምን ለማጽናት የተከናወኑ ተግባራት ውጤት ማስገኝታቸውንም አንስተዋል። የተቋሙን የወንጀል መከላከል ሥራ በደኅንነት ካሜራዎች ጭምር በቴክኖሎጂ በመደገፍ ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን ነው የተናገሩት።
በከተማው የተተከሉ የደኅንነት ካሜራዎች በክልሉ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በመከታተል ወንጀል ከመከሰቱ በፊት ቀድሞ ምላሽ ለመስጠት ከማስቻሉ ባለፈ የምርመራ ሥራዎችን እያቀለሉ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ የኮትሮባንድ ንግድን ጨምሮ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በተሠራው ተግባር አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።
ከ73 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ጠቅሰዋል።
በተለይ በክልሉ ሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይትን ለማስቆም በተሠራው ተግባር ከ14 ሺህ ሊትር በላይ በሕገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ ነዳጅን ከነ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ብለዋል።
በሌላ በኩል ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በተሠራው ሥራ ከሀገር ሊኮበልሉ የነበሩ ሰዎችን ከነ አስኮብላዮቻቸው በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ገልጸዋል።
በመሠረተ ልማቶች ላይ በተለያዩ አከባቢዎች ስርቆት ሲፈጽሙ የነበሩ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አንስተዋል።
በሕገ ወጥ የባጃጅ ስርቆት ላይ የተሳተፍ አካላትንም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም በክልሉ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ወደ አስተማማኝ ሰላም ለማሳደግ ማኅበረሰቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ የተጀመሩ የሰላም እሴት ጥበቃ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
#CommunityPolicing #TechForSecurity #Harar
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_13_2018_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
