
የአርንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ሊያሳድጉ የሚችሉ ችግኞች በስፋት እንዲተከሉ ዕድል ፈጥሯል፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደርም ከደን ችግኞች በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በተለይ ቡና፣ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና ሌሎች ችግኞች እንዲተከሉ እያደረገ ይገኛል፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ ቤዛዊት ጌታሁን ለአሚኮ አንደገለጹት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን ለመትከል በስፋት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡የአርንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከቡና ችግኝ ጋር በማስተሳሰር መሥራት ከተጀመረ ወዲህ ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ብቻ ከ10 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ በመግሥት ችግኝ ጣቢያዎች እና በግለሰቦች ተፈልተው ለተከላ ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት፡፡ እስከ አሁን ድረስም በርካታ ቁጥር ያላው የቡና ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደሮች ጋር በተደጋጋሚ ውይይቶች ከተደረጉ በኋላ አንድ አርሶ አደር ከራሱ ማሳ ከግማሽ ሄክታር እስከ 1 ነጥብ 5 ሄክታር ድረስ በቡና ችግኝ እየሸፈነ እንደኾነም አንስተዋል፡፡ ቡና የማልማት ተሞክሮውም ልምድ እየኾነ መጥቷል ብለዋል፡፡
ጀንፈል እና የታጠበ ቡና በመሸጥ አርሶ አደሮች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ኾነዋል ያሉት ኀላፊዋ እያንዳንዱ ቀበሌ ከ40 እስከ 100 ሄክታር በኩታገጠም የቡና ችግኝ እንዲተክል እየተደረገ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው በክልል ደረጃ 37 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡
25 ሺህ ሄክታር የሚኾን ማሳ ላይ ያለው የቡና ተክል ምርት እየሰጠ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡በተለይ በ2017/18 የምርት ዘመን 170ሺህ ኩንታል የቡና ምርት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ከሚለማው 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ በቡና የለማው 37ሺህ ሄክታር ብቻ በመኾኑ አሁንም በትኩረት መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም የቡና ችግኝ አንዱ የትኩረት ማዕክል ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
#አሚኮ #GreenLegacy #CoffeeProduction #AmharaRegion
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_13_2018 ዓ_ም
ዘጋቢ፡-ሰለሞን ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
