የሥልጣን ጥማቱን ለማርካት የትግራይ ሕዝብን ረግጦ መግዛት የሕገወጡ ሕወሃት ፍላጎት ነው።

25

 

የፕሪቶሪያን የሰላም ሥምምነት ያፈረሰው ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን የትግራይ ሕዝብን ዳግም በሀሰት ፕሮፖጋንዳዎቹ ለማታለል እየሠራ እንደሚገኝ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ።

መንግሥት የትግራይ ክልልን መልሶ ለማቋቋም ለክልሉ በጀትን ከመመደብ ጀምሮ አያሌ ተግባራትን ማከናወኑ ይታወሳል። ኾኖም ግን መንግሥት ለዘላቂ ሰላም ቁርጠኝነት እያከናወነ የነበረውን ተግባር በማደናቀፍ ሕገ ወጡ ቡድን የፕሪቶሪያውን ውል በይፋ አፍርሷል።

ታጣቂዎችን ወደ ተሃድሶ ኮሚሽን ባለማሥገባት፤ ከውጭ እና ከውስጥ ታጣቂዎች ጋር በመጣመር፤ ሉዓላዊነቷን በመጋፋት፤ በፕሪቶሪያው ውል መሠረት የተቋቋመውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሥተዳደር በኃይል በማፍረስ እና የራሱን ሕገወጥ መዋቅር በመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መኾኑ ይታወቃል። ለጦርነት ዝግጅት በማድረግ፤ ወጣቶች ላይ አፈና በመፈጸም ወደ ጦርነት ማሠልጠኛ በመውሰድ፤ አስገዳጅ አዋጅን በማጽደቅ፤ ሌሎች ተግባራትን በመፈጸም ላይ ይገኛል።

ይህ የጥፋት ሤራው ተጋልጦበት በዓለም አቀፍ ዘንድ እገዳ እና ማስጠንቀቂያ እየተሰጠውም ይገኛል። የራሱን ጥፋት ባለመቀበል የትግራይ ሕዝብን ተከድተሃል፤ ልትጨፈጨፍ ነው፤ በጀትህ ተከልክሏል፤ የዘር ማጥፋት ሊፈጸምብህ ነው በማለት የትግራይን ሕዝብ በሀሰት መረጃ እያታለለም ይገኛል።

በፕሪቶሪያ ውል መሠረት የተቋቋመውን የክልሉን መዋቅር አፍርሶ በኃይል ራሱን መዋቅር የዘረጋው ቡድን የሕገ ወጡ ቡድን የትግራይ ሕዝብ ጀኖሳይድ ሊፈጸምብህ ነው ተዘጋጅ እያለ የጦርነት ቅስቀሳ እያደረገ ነው።

ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ከሰሞኑ ባስተላለፈው መልዕክት በፕሪቶሪያ ውል የተቋቋመውን የክልሉን መዋቅር በማፍረስ የራሱን መዋቅር በኃይል መዘርጋቱን እና ሥልጣን መቆጣጠሩን ሲገልጽ ተስተውሏል።

የሕገ ወጥ ቡድኑን ሴራ የተረዱ ወጣቶች በዕኩይ ሴራው ላለመሳተፍ ቢሞክሩም አፈና እየተፈጸመባቸው መኾኑን ከሰሞኑ ከትግራይ ክልል የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። የሕዝቡን ተቃውሞ በተለያዩ አዋጆች በማሥፈራራት በግድ እንዲቀበሉት እያደረገም ይገኛል።

ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ተንታኝ እና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረ ማርያም ሕገ ወጡ ቡድን የፕሪቶሪያን ውል በማፍረስ፤ አስገድዶ በማፈን የሰዎችን መብት በመንጠቅ፤ ሕጻናትን ወደ ጦርነት እንዲገቡ በማስገድድ የሀገሪቱን እና የዓለም አቀፍ ሕግን መጣሱን ገልጸዋል።

የሥልጣን ጥማቱን ለማርካት የትግራይ ሕዝብን ረግጦ መግዛት የቡድኑ ፍላጎት መኾኑንም ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመኾን ጦርነትን ለመክፈት እየተቀሳቀሰ ነው ብለዋል። በሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ሕዝቡን ለማታለል እየሠራ መኾኑንም አብራርተዋል። “ንጹሐንን ይጨርሳሉ እንጅ ኢትዮጵያን ማፍረስ አይችሉም” ነው ያሉት።

የፕሪቶሪያ ስምምነትን ያለቅድመ ሁኔታ መፈጸም፤ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ችግሮች እንዲፈቱ መፍቀድ፤ ሰላምን በማስቀደም በሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን ማጽናት፤ የትግራይ ሕዝብን ዘላቂ ሰላም ማስቀደም ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ሊወስደው የሚገባ የመፍትሔ ተግባር መኾኑንም ተናግረዋል።

የትግራይ ምሁራን የሕገ ወጥ ቡድኑን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በማጋለጥ፤ ሕዝቡን በማንቃት እና ጦርነትን በማውገዝ ሰላምን ማስቀደም ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ መንገድ ሰላማዊ ነው፤ ለሰላም በሩ ክፍት ነው፤ ሕገ ወጡ ቡድን እና ሌሎች ታጣቂዎችም የሰላምን መንገድ ሊከተሉ ይገባል ብለዋል።

#አሚኮ_ዜና #የፕሪቶሪያስምምነት🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_13_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበሶማሌ ክልል ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማሳለጥ አዲስ የፈጠራ ማዕከል በይፋ ሥራ ጀመረ።
Next articleበዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለቡና ችግኝ ትኩረት ተሰጥቷል።