በሶማሌ ክልል ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማሳለጥ አዲስ የፈጠራ ማዕከል በይፋ ሥራ ጀመረ።

10

 

በሶማሌ ክልል የወጣቶችን የፈጠራ ችሎታ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ይበልጥ ለማጎልበት ታሳቢ ያደረገ አዲስ የኢኖቬሽን ማዕከል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል።

ማዕከሉን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ያደረጉት የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ሙስጠፋ መሐመድ ናቸው። መንግሥት በክልሉ አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን እና የዲጂታል ኢኮኖሚን ለማሳለጥ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን በዕለቱ ገልጸዋል።

ይህ አዲስ የኢኖቬሽን ማዕከል በቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቁ እና ተወዳዳሪ የኾኑ ዜጎችን ለማፍራት እንዲሁም የወጣቶችን አቅም ለመገንባት ሰፊ ዕድል የሚፈጥር መኾኑን ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል።

መንግሥት ለቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት ሳቢያ አበረታች ለውጦች እየተመዘገቡ መኾኑን ነው የገለጹት። በቀጣይም ማዕከሉን በዘመናዊ ግብዓቶች እና በባለሙያዎች የማጠናከር ሥራ በትኩረት እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የክልሉ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኀላፊ መሐመድ አሊ ማዕከሉ ወጣቶች ያላቸውን የፈጠራ ክህሎት በተግባር የሚያሳድጉበት ስትራቴጂካዊ ተቋም መኾኑን ተናግረዋል።

ይህ ማዕከል የተመሠረተው የሀገሪቱን እና የክልሉን የ2030 የዲጂታል ስትራቴጂ ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ ታሳቢ ተደርጎ መኾኑን ያብራሩት ኀላፊው ተቋሙ በቀጣይ ለወጣቶች እና ለፈጠራ ባለሙያዎች ሰፊ የቴክኖሎጂ ሥልጠናዎችን እና ድጋፎችን እንደሚያቀርብም ከሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በዚህም መሠረት ማዕከሉ በድረ ገጽ ልማት፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በመረጃ ትንተና፣ በሳይበር ሴኩሪቲ እና በዲጂታል ዲዛይን አገልግሎት በመሳሰሉት ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥም ተነስቷል።

#Jigjiga #SomaliRegion #InnovationCenter
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_13_2018_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበአማራ ክልል ከ126 ሺህ በላይ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ።
Next articleየሥልጣን ጥማቱን ለማርካት የትግራይ ሕዝብን ረግጦ መግዛት የሕገወጡ ሕወሃት ፍላጎት ነው።