
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ንግድን እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዮናስ መላኩ በ120 ሚሊዮን ብር ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ተገንብቶ ወደ ሥራ በመግባቱ ከ340 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል።
በከተማው ሕገ ወጥ ንግድን በመቆጣጠር ገበያውን ማረጋጋት ተችሏልም ብለዋል። በበጀት ዓመቱ 1 ሺህ 240 ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱንም ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዳንኤል ወርቁ በዞኑ በገበያ ማዕከላት፤ በድንኳን ገበያ እና በሌሎችም አማራጮች ምርት በስፋት በማቅረብ ገበያውን ለማረጋጋት ሰፊ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
ሕገ ወጥነትን ለመከላከል ወደ 72 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ተመድቦ ገበያውን ለማረጋጋት ጥረት ተደርጓል፤ በዚህም ውጤት አግኝተንበታል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሒም ሙሐመድ (ዶ.ር) አሠራርን በማዘመን፤ የገበያ ማዕከላትን በማስፋት፤ ምርትን በማሠራጨት፤ ሕገ ወጥ ንግዶችን በመቆጣጠር እና በሌሎች ዘርፎች በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ ሕገ ወጥ ንግድን በመከላከል ገበያውን ለማረጋጋት በትኩረት ሢሠራ ቆይቷልም ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ከ126 ሺህ በላይ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ አሥተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ14 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርት የገበያ ትስስር በመፍጠር ገበያውን ለማረጋጋት ተሠርቷል ብለዋል።
ሕገ ወጥ ንግድን በመከላከል ገበያውን ለማረጋጋት በተደረገው ጥረት የተገኘው ውጤት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።
#አሚኮ_ዜና #ሕገወጥንግድ
#ደሴ #ሐምሌ_13_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ መስዑድ ጀማል
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
