
ዋልያ በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ብቻ የሚገኝ ብርቅዬ እንሰሳት ነው። ይህ እንሰሳት የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ ኾኖ እንዲመዘገብ ካስቻሉት የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል ዋልያ ግንባር ቀደሙ ነው።
ይህ መኖሪያውን ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያም በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ብቻ ያደረገው ብርቅዬ እንሰሳት ከሌሎች እንሰሳት አኳያ ሲታይ በቁጥር አነስተኛ ነው። ይባስ ብሎ በግጭቶች የተነሳ አሁን ላይ ከነበረው ቁጥር በእጅጉ መቀነሱ ይታወሳል።
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ተወካይ ኀላፊ ላቀው መልካሙ እንደተናገሩት የዋልያ ቁጥር ከ 2013 ዓ.ም ጀምሮ በነበረው ጦርነት በተፈጠረው የሕግ መላላት ለተለያዩ አደጋዎች ተጋልጦ ነበር። ቁጥሩም ከነበረበት 638 ወደ 306 መቀነሱን ተናግረዋል። ጽሕፈት ቤቱም በ2016/17 ዓ.ም በዋልያ ላይ የተፈጠረውን ችግር እና ቁጥራቸው መቀነሱን ለሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ማሳወቁን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የተፈጠረውን ችግር በመለየት ለመቆጣጠር ከስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት እና ከሌሎች ጋር በመኾን በ2016 ዓ.ም ጥናት ማካሄዱን አንስተዋል። በጥናቱም በተፈጠረው የሕግ መላላት የዋልያዎች መኖሪያ አካባቢ በሰዎች በመረበሹ የነበሩበትን ምቹ መኖሪያ በመልቀቃቸው ለአደን ተጋላጭ እንደኾኑ ተለይቷል ነው ያሉት።
በጥናት ከተለየ በኋላ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር ተደርጎ የዋልያውን ቁጥር ወደነበረበት ለመመለስ የአስር ዓመት ስትራቴጅ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰዋል። ዋልያዎች በሚገኙበት አካባቢ አሰሳ እና ቅኝት የማድረግ፤ የዋልያ አምባሳደሮች በሚል 12 አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ ሌት ተቀን ቅኝት በማድረግ የዋልያዎችን ውሎ አዳር የመከታተል፤ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ተከናውኗልም ብለዋል። ማኅበረሰቡም ለዋልያዎቹ ከፍተኛ ከለላ እየኾነ መኾኑን ተናግረዋል። በተከናወነው ሥራም ባለፈው አንድ ዓመት ሕገ ወጥ እንቅስቃሴውን በመቆጣጠር ምንም ዓይነት የአደን እንቅስቃሴ እንዳይኖር ተደርጓል ነው ያሉት።
ኾኖም ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ኅብረት የተሰኘው መንግሥታዊ ያልኾነ ድርጅት በ 2016/2017 ዓ.ም በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት የደረሰውን ጥናታዊ ሪፖርት በማየት በቅርቡ “ዋልያ በጣም አሳሳቢ የመጥፋት አደጋ ውስጥ በመኾኑ ከፍተኛ ትኩረት ይፈልጋል” በሚል በራሱ ተቋም የአደጋ መዝገብ ውስጥ አስገብቶታል ብለዋል።
ይሁንና ዋልያ በድርጅቱ የአደጋ መዝገብ ውስጥ መካተቱ በመጥፎ አናየውም ብለዋል ነው ያሉት። በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እንዲያገኝ፣ የገንዘብ ድጋፎች እንዲገኙ እና ፓርኩን በዘላቂነት ለመጠበቅ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
የዋልያ ቁጥር ሲቀንስ ይህ የመጀመሪያ አለመኾኑን የጠቀሱት ተወካይ ኀላፊው ከዚህ ቀደምም በ1983 አካባቢ በነበረው ጦርነት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ለአደጋ ተጋላጭ በሚል ተመዝግቦ እንደነበር አስታውሰዋል። በወቅቱ በተከናወነው የጥበቃ እና የእንክብካቤ ሥራ ቁጥሩ ወደነበረበት ተመልሶ ከአደጋ ተጋላጭ መዝገቡ መውጣት ችሏል ነው ያሉት።
ያለፉትን ጊዜያት ልምድ መነሻ በማድረግ መኖሪያ አካባቢያቸውን ከሰዎች እንቅስቃሴ በመጠበቅ ምቾት እንዲሰማቸው በማድረግ በቀላሉ እንዲራቡ እና ቁጥራቸው እንዲጨምር ማድረግ ይቻላል ብለዋል። በአንዳንድ አካባቢ እስከ 15 የሚደርሱ ግልገሎች እንደታዩ በመጥቀስም አሁንም በመራባት ላይ መኾናቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የዓለም ቅርስ ነው፤ ኹሉም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት። መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶችም በገንዘብ ድጋፍ እና በጥናታዊ ምርምሮች ሊያግዙ እንደሚገባም ጠይቀዋል።
#አሚኮ #WaliaIbex #SimienMountains #WildlifeConservation #EndangeredSpecies
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_13_2018 ዓ_ም
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
