🚢 “ኢራን የሆርሙዝን ወሽመጥ እንደ መደራደሪያ ካርድ ልትጠቀምበት ትፈልጋለች” ማርኮ ሩቢዮ

9

 

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ካለው ግጭት አኳያ ኢራን የሆርሙዝን የባሕር ላይ መተላለፊያ እንደ መደራደሪያ ልትጠቀምበት እየሞከረች ነው ብለዋል። ሌሎች ሀገራት ዓለም አቀፍ የባሕር ላይ መጓጓዣ መስመሮችን በመጠበቅ ረገድ የላቀ ሚና እንዲጫወቱም አሳስበዋል።

የደቡብ ምሥራቅ እስያ ሀገራት ማኅበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሥብሠባ ላይ ለመሳተፍ ወደ ፊሊፒንስ ከማቅናታቸው በፊት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፣ “ኢራናውያን ባሕረ ሰላጤውን በመቆጣጠር በዓለም ላይ እንደ ተጽዕኖ መፍጠሪያ ሊጠቀሙበት እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው” ብለዋል።

አሜሪካ የዓለም አቀፉን የባሕር ላይ ንግድ ደኅንነት ለማረጋገጥ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰዷን የምትቀጥል ቢኾንም ሌሎች ሀገራትም የገንዘብ ድጋፍ ወይም ወታደራዊ ግብዓትን በማቅረብ ሸክሙን በመጋራት በኩል የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አክለዋል።

ዋሽንግተን ከኢራን ጋር ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ላይ ለመድረስ ቁርጠኛ መኾኗን ሩቢዮ ተናግረዋል። ዲፕሎማሲው ካልተሳካ ግን ሁኔታው ለቴህራን የሚጠቅም እንደማይኾን አስጠንቅቀዋል። ኢራናውያን ከአሜሪካ ጋር ለመነጋገር ፍላጎት እንዳላቸው ምልክቶች እየታዩ መኾኑን ሩቢዮ መናገራቸውን አናፎፈዶሉ የዜና አውታር ዘግቧል።

#አሚኮ #HormuzStrait #Iran

#ባሕር_ዳር ሐምሌ_13_2018 ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“በመሳሪያ የሚፈታ ችግር የለም፤ ችግሮች በምክክር እንዲፈቱ የምክክር ኮሚሽኑ አንድ አካል እንሁን” ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ
Next articleበዋልያ ላይ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ማስቆም ተችሏል።