
በዓለም ላይ ታሪክ የተከሰቱ ጦርነቶች በአብዛኛዎቹ የመጨረሻ መዳረሻቸው ሰላማዊ ሥምምነት ማድረግ ነው። በተለይ በሀገር ውስጥ የሚፈጠር የእርስ በእርስ ግጭቶች ሰብዓዊ ጉዳትን አድርሰው፤ መሠረተ ልማቶችን አውድመው፤ የንጹሐንን ሕይወት ቀጥፈው፤ የበርካቶችን አካል አጉድለው፤ በሀገሪቱ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ኪሳራ አድርሰው በመጨረሻም በሰላም ስምምነት ይጠናቀቃሉ።
ከብዙ ውድመት እና ኪሳራ፤ ከሞት እና ከአካል መጉደል በኋላ ሰላም ይሰፍናል። የታደሉት በሕይወት ሲቆዩ በርካታ ቤቶች ግን ኦና ይኾናሉ።
በጦርነት ልጆቿን ያጣች እናት በር ላይ እያነባች ትጠብቃለች፤ ልጆቹን ያጣ አባት በደከሙ አይኖቹ ጧሪዎቹን ይፈልጋል፤ አባታቸውን ጦርነት የበላባቸው ሕጻናት የጎዳና ተዳዳሪ ይኾናሉ።
ከጦርነቱ በፊት የሰላምን ጥቅም ያልተረዱ በርካቶች ጦርነት እና ግጭት ያደረሰባቸውን ጥልቅ ሥብራት ከጉዳት በኋላ ይማሩበታል፤ በቀሪ ዘመናቸው ሰላምን ይሰብካሉ።
በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ዘርፈ ብዙ ጉዳትን አስከትሏል። በክልሉ ሕዝብ ላይ የደረሰውን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና፤ የሕዝቡን ሰቆቃ የተረዱ በርካታ ታጣቂዎች ከትጥቅ ትግል በመውጣት የሰላምን አማራጭ ተቀብለዋል። የሰላም ትሩፋትን ተገንዝበዋል።
የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎችም ችግሮችን ከኢትዮጵያ ወንድም እና እህቶቻቸው ጋር በጋራ ሊፈቱ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ላይ እየተሳተፉ ነው።
ከትጥቅ ትግል በመውጣት እና የሰላምን አማራጭ በመቀበል በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት፤ በምክክር እና በውይይት ሀገር የምትቀጥልበት፤ ችግሮች ተቀንሰው ተስፋዎች የሚቀጥሉበት፤ ሁሉም ብሔረሰቦች የሚሳተፉበት፤ ሁሉም በዕኩል ድምጽ የሚወስንበት መድረክ መኾኑን ተናግረዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጉባኤን ለማጠልሸት የሚሞክሩ፤ መልካም ጎኑ የማይታያቸው ሰዎች ወደ ልቦናቸው በመመለስ መልካም ነገሩን እንዲመለከቱ እና አሻራቸውን እንዲያስቀምጡም አሳስበዋል።
የሚመለሱ ጥያቄዎች እና መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች በውይይት እንዲፈቱ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አንድ አካል እንዲኾኑም ጥሪ አቅርበዋል።
በመሳሪያ የሚፈታ ችግር የለም፤ በውይይት እና በንግግር የሕዝብን ጥያቄ ማስመለስ ይገባል ነው ያሉት። የውጭ ጣልቃ ገቦችን የምንቆርጥበት መንገድ በመኾኑ ሁሉም ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።
#አሚኮ_ዜና #ሀገራዊምክክር #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_13_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
