በአማራ ክልል የኮሪደር ልማቱ 200 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

12

 

​በአማራ ክልል የሚገኙ ከተሞችን ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፉ የማድረግ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ እንደሚገኙ የከተማ ክላስተር ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ አማካሪ ሽቤ ክንዴ እንደተናገሩት በክልሉ የሚገኙ ከተሞችን የማዘመን እና ተወዳዳሪ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

ከተሞችን ጽዱ እና ውብ ለማድረግ የመንገድ ግንባታ፣ የአረንጓዴ ስፍራ፣ እና የጭቃ ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን አብራርተዋል።

በ2018 በጀት ዓመት ሰፊ የኮሪደር ልማት ሥራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል። የእግረኛ፣ የብስክሌት መንገዶች፣ የካሜራ፣ የስማርት ፖል ተከላ፣ የአረንጓዴ ልማት እና የመኪና ማቆሚያዎች ግንባታ በኮሪደር ልማቱ ትኩረት የተሰጣቸው ስለመኾኑም አስረድተዋል።

በበጀት ዓመቱ በክልሉ በመንግሥት እና በኅብረተሰቡ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ የኮሪደር ልማት ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። በዚህም በኮሪደር ልማቱ 199 ሺህ 785 ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኀላፊ የቻለ ይግዛው እንደገለጹት በክልሉ የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የሞሰብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በስፋት ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

እስካሁን በክልል ደረጃ የተገነባውን ዋናውን ማዕከል ጨምሮ በባሕር ዳር፣ ደሴ እና ወልዲያ ከተሞች አገልግሎቱ መጀመሩን አንስተዋል። የጎንደር፣ የደብረ ታቦር፣ የኮምቦልቻ እና የደብረ ብርሃን ከተሞች ደግሞ በቀጣይ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ጠቁመዋል።

በ2018 ዓ.ም በክልሉ ከ6 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል። በቀጣይ ከ12 ሚሊዮን በላይ የገጠር ነዋሪዎችን እና ከ650 ሺህ በላይ የከተማ ነዋሪዎችን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ እየተሠራ ነውም ብለዋል።

በኢትዮ-ኮደርስ ሥልጠና እስከ አሁን ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሠልጥነው ሰርትፍኬት ማግኘታቸውንም ተናግረዋል። ይህም ጥሩ ውጤት የተገኘበት እና ተጠናክሮ የሚቀጥል መኾኑን አመላክተዋል።

#አሚኮ #AmharaRegion #UrbanDevelopment

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 13/2018 ዓ.ም

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🌍 ለእኛ የመጀመሪያ፤ የዓለም ሀገራትን ከቀውስ ያወጣ የሰላም ጋሻ – ሀገራዊ ምክክር 🕊️
Next article“በመሳሪያ የሚፈታ ችግር የለም፤ ችግሮች በምክክር እንዲፈቱ የምክክር ኮሚሽኑ አንድ አካል እንሁን” ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ