
ኢትዮጵያ በመላው ልጆቿ ደም እና አጥንት የቆመች ሀገር ናት። ለሉዓላዊነቱ ደሙን ያፈሰሰ፤ አጥንቱን የከሰከሰ ሕዝብ ደግሞ በሀገሩ ጉዳይ ዳር ተመልካች መኾን አይገባውም።
ይሁን እና ያለፉትን በርካታ ዓመታት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ታሪክ ሲፈተሽ ከዚህ ፍጹም በተቃራኒ የተቃኜ ነበር። በሀገር ጉዳይ የሕዝብ ፍላጎት እና መብት ወደ ጎን ተጥሎ የኢትዮጵያ መፃዒ ዕድል “እኛ ካላወቅንላችሁ” በሚሉ ጥቂት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በጣት በሚቆጠሩ የፖለቲካ ልሂቃን ጠባብ ፍላጎት ተሸፍኖ ቆይቷል። ይህ ሰፊውን ሕዝብ ያገለለ የፖለቲካ አካሄድ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ብልጽግና ከመውሰድ ይልቅ ለከፋ ማኅበራዊ ቀውስ ዳርጓት ቆይቷል።
በእነዚያ ጊዜያቶች የፖለቲካ ፓርቲዎች መዋቅር እና ሥልጣን የሕዝብን ውክልና የሚያረጋግጡ ሳይኾኑ ጥቂት ግለሰቦች የራሳቸውን ጥቅም የሚያስጠብቁባቸው መሣሪያዎች ነበሩ።
በእነዚያ ጊዜያቶች የሀገር እጣ ፋንታ የሚወሰነው በሕዝባዊ ምክክር እና በጋራ ስምምነት ሳይኾን ከሕዝብ ዕይታ በራቁ ዝግ መድረኮች በሚደረጉ የፓርቲ መሪዎች ስምምነቶች እና ውሳኔዎች ነበር።
በእነዚያ ሥርዓቶች የፖለቲካ ሥርዓቱ አካታች እና የብዙኀኑን ፍላጎት የማያንፀባርቅ ስለነበር የሀገሪቱ የሥልጣን ሽግግር እና የፖለቲካ ሂደት ሁልጊዜም በኀይል እና በግጭት የታጀበ እንዲኾን አድርጎታል። ይህም ትርፉ የሰፋ ልዩነት፣ ግጭት እና አለመረጋጋት ብቻ እንዲኾን አድርጎታል።
አሁን የኢትዮጵያ መፃዒ ዕድል አስተማማኝ ሊኾን የሚችለው ሰፊው ሕዝብ ያለ ምንም ልዩነት በቀጥታ እና በነፃነት በሀገሩ ጉዳይ መወሰን ሲችል ብቻ መኾኑን ታሪክ አስተምሮናል። የተገኘው ትምህርትም ሀገራዊ የምክክር ጉባኤውን ወልዷል። ምክክሩ የቆየውን አጥፊ የፖለቲካ አካሄድ የቀየረ እና የመላው ኢትዮጵያውያንን የጋራ ድምጽ እና ባለቤትነት በተግባር አረጋግጧል።
ይሁን እና አሁንም “እኛ ካላወቅንላችሁ” ከሚለው የፖለቲካ አካሄዳቸው ያልተላቀቁ አካላት ራሳቸውን ከምክክሩ በማግለል በኋላም አሳታፊ አይለም በማለት በምክክር ጉባኤው ላይ የተለያዩ አቃቂሮችን ማውጣት ጀምረዋል። “ከምክክሩ በኋላ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች” የሚል ከንቱ ምኞታቸውን በማራገብም የኢትዮጵያ ጠላቶች መኾናቸውን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያውያን በአንድ ልብ መክረው፤ በአንድ ቃል ተናግረው ከጀመሩት የምክክር ሂደት ለማደናቀፍ እና ለማጣጣል ሌት ከቀን የሚሠሩት እነዚህ አካላት ታሪካዊ መነሻቸው ሲመረመር ሁልጊዜም ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር አብሮ በመሰለፍ የሚታወቁ ናቸው።
ነገር ግን የምክክር ጉባኤው መላው ኢትዮጵያውያን እየተሳተፉበት የሚገኝ እና ትልቅ የአንድነት እና የሰላም ተስፋ የተሰነቀበት መኾኑን በምክክሩ እየተሳተፉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ ኀላፊዎች አረጋግጠዋል።
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሠብሣቢ እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኀይሎች ንቅናቄ (አዴኀን) ሊቀመንበር ተስፋሁን ዓለምነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ሂደት የጥቂቶች ማሸነፊያ ሳይኾን የሁላችንም የጋራ ተስፋ መገንቢያ መድረክ ነው” በማለት በምክክሩ ኹሉም ኢትዮጵያውያን እየተሳተፉ መኾናቸውን አረጋግጠዋል።
ልዩነቶቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ በማምጣት፤ በመደማመጥ እና በሀሳብ ብልጫ የምንፈጥረው አዲስ መንገድ ማንም የማይሸነፍበትን፤ ሁላችንም እኩል አሸናፊ የምንኾንባትን ኢትዮጵያን ይወልዳል በሚል ተስፋ እየተሳተፉ መኾናቸውን በመግለጽ በምክክሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ተሳታፊ መኾናቸውን አረጋግጠዋል።
በምክክሩ በትግል ወቅት የነበሩ ጥያቄዎችን ወደ መድርክ እንዳቀረቡ በማንሳት ታሪካዊ አጋጣሚው ለነገው ትውልድ ትልቅ የአንድነት፣ የፍትሕ፣ የመግባባት፣ የሰላም እና የመሠልጠን ስጦታ እንደሚኾንም ነው የተናገሩት።
#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ12/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
