
አንድን ሀገር ሀገር የሚያሰኛት የድንበር መስመር ወይም የመሬት ስፋት ብቻ አይደለም። በውስጧ የሚኖሩ ሕዝቦች በጋራ የገነቡት ታሪክ፣ የተጋሩት ዕጣ ፈንታ፣ የደሙለት ሰንደቅ ዓላማ እና በክፉም በደጉም አብረው የቆሙበት የሕልውና ትስስር ጭምር እንጂ።
ባለፉት ዓመታት ግን በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የተከሰተው ፖለቲካዊ ተውኔት ይህንን እውነት የሚክድ ነው። ሀገርን የሚያፈርሱ እና ሕዝብን የሚያናቁሩ አደገኛ አጀንዳዎች ሲስተናገዱ ቆይተዋል። ለዚህ አፍራሽ ሚና ደግሞ በዋና ተዋናይነት የሚጠቀሰው ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ነው።
ቡድኑ ሥልጣን ላይ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ያሳየው አካሄድ በአንድ ግዙፍ ጥያቄ ፊት እንድንቆም ያደርገናል። የቡድኑ አባላት ኢትዮጵያ ምን ብታደርጋቸው ነው ይሕን ያህል ከሰፈራቸው በታች ለማድረግ የተነሱት? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።
🛑 የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አውታሮች፣ የውጭ ብድር እና እርዳታዎችን በጥቂት የቡድኑ አባላት እና ቤተሰቦቻቸው እንደ ኤፈርት ባሉ ተቋማት ሥር በማከማቸት ሀገርን የመመዝበሪያ ማሽን አድርጎታል። ከሥልጣን ሲወገድም ሀብት በማሸሽ እና በማውደም ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ሽባ ለማድረግ ሞክሯል።
የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የተፈጸመው የጀርባ ክህደት ጥቃትም በታሪክ አቻ የማይገኝለት የወገን ጭካኔ ማሳያ ነው።
የኢፌድሪ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ በተለያዩ ጊዜያቶች ሲያወጧቸው እንደነበሩ የመስክ ምልከታ መግለጫዎች በአማራ እና አፋር ክልሎች በንጹሐን ላይ የደረሰው ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና የመሠረተ ልማት ውድመትም የቡድኑን ለወገኑ የማያስብ መኾኑን ማሳያ ነው።
ሀገር ለማፍረስ የራስን ታጣቂ ኃይል መገንባት፤ ከማዕከላዊ መንግሥት እውቅና ውጪ ምርጫ ማካሄድ እና ሀገሪቱ ስትፈራርስ የራስን ብቸኛ ነጻነት ለማወጅ የተደረገ ቅድመ ዝግጅትም ነበረ። ምንም እንኳን ዛሬም ተስፋ ባለመቁረጥ እየሞከረ ቢኾንም።
🤝 ትልቁ እና ወሳኙ ነጥብ ግን ሕወሃት ማለት የትግራይ ሕዝብ፤ የትግራይ ሕዝብ ሕወሃት አለመኾኑን መለየት ነው። የአንድ ቡድን የሥልጣን ጥማት መላውን የትግራይ ሕዝብ ሊወክል አይችልም። የትግራይ ሕዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ ወንድም እና እህቱ ጋር በጋብቻ፣ በሃይማኖት፣ በባሕል እና በታሪክ የተሳሰረ ነው።
ቡድኑ ግን የትግራይን ሕዝብ ከእኔ ውጭ ሌላው ጠላትህ ነው በሚል የፍርሃት እና የጥርጣሬ ፖለቲካ በመርጨት የራሱ ሰለባ ለማድረግ ጥሯል። ብዙ የትግራይ እናቶች ግን ልጆቻቸው የጦርነት ማገዶ እንዲኾኑ አይፈልጉም። ያለፈውን ጊዜ ለተረዳው በብዙ የሚያስተምር ነውና።
🇪🇹 አሁን ያለንበት ወቅት እውነትን ከሐሰት ለይተን የምንቆምበት ጊዜ ነው። ትግሉ ከሕዝብ ጋር ሳይኾን ከአፍራሽ ሐሳቦች ጋር መኾንም አለበት። ኢትዮጵያን ዳግም አታቁስሏት ሊባሉ ይገባል። የትግራይ ሕዝብ ከመላው ኢትዮጵያ ጋር በጋራ የመኖር ፍላጎት እንዳለው በመገንዘብ ካሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ይላቀቁ ዘንድ በአይዟችሁ መንፈስ እጃቸውን መደገፍ ይገባል።
ኢትዮጵያ ለሁሉም ልጆቿ የምትበቃ፣ በፍቅር እና በፍትሕ የምትመራ ሀገር ልትኾን የምትችለው እንዲህ ያሉትን ከፋፋይ እና በዝባዥ ኃይሎች በጋራ መታገል ሲቻልም ነው። የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት አካል ነውና ይህን አካል ቆርጦ ለመጣል የሚሞክረውን የጥፋት መንገድ በጋራ ማረም እና አጥፊዎቹ ከጥፋታቸው ተመልሰው ከራሳቸው አልፎ ስለ ወገናቸው እና ሀገራቸው እንዲያስቡ ማድረግም ከመላው ኢትዮጵያ ትልቅ ሥራ ይጠበቃል።
💬 ውድ ኢትዮጵያውያን እናንተስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ትላላችሁ? ሀሳባችሁን አጋሩን 👇
#ኢትዮጵያ #አንድነት #ሰላም #ባሕር_ዳር #ሐምሌ11_2018ዓ_ም (አሚኮ)
✍️ በሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
