👩‍👧‍👦🕊️አራስነት ያልገደበው የእናቶች የሰላም መሻት፣በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ

14

​ሰሞኑን በታላቅ ድምቀት የተጀመረው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር እድል ይዞ እንደሚመጣ ተስፋ ተጥሎበታል። ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያውያንን የጋራ ዕጣ ፈንታን የሚወስን ታሪካዊ አጋጣሚ ተደርጎ ተወስዷል።🇪🇹

በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ በሕዝብ የተመረጠ ሁሉ በተወካይነት ተገኝቷል። ሽማግሌዎች ድካማቸውን ዋጥ አድርገው፣ የታመሙት ሕመማቸውን ችለው፣ የወለዱት አራስነታቸውን ​ታግሰው፣ ነፍሰ ጡር እናቶች ምቾታቸውን ትተው በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል።

​የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ጥልቅ ትርጉም የሚገለጸው በዜጎች ፍጹም ቅንነት እና መስዋዕትነት ላይ ጭምር የተመሠረተ መኾኑ ነው። ለዚህም ማሳያ ከጉባኤው አዳራሽ አንድ ልብ የሚነካ ምስክርነትን ልናጋራችሁ ወደድን። 👇

✍️ለጉባኤው የተከፈለ ዋጋ፣ የእናቶች መሻት

በጉባኤው አዳራሽ ውስጥ የብዙዎችን ቀልብ የሳበው እና የሰላምን ውድነት በተግባር ካሳየው አጋጣሚ መካከል የአራስ እናቶች መገኘት አንዱ ነበር።

አንደኛዋ እናት ገና የሁለት ወር ጨቅላ ሕፃን ልጃቸውን አቅፈው በምክክሩ ላይ ተገኝተዋል። ​እኒህ እናት የአራስነት ጉልበታቸው ሳይጠና፣ ድካም እና ህመም ሳይበግራቸው ሕፃን ልጃቸውን ታቅፈው ነው የተገኙት።

የመጡበትን ዓላማ ሲያስረዱም ​”የመጣነው ሰላም ፈልገን ነው፤ ሀገራችን ሰላም ናፍቋታል፤ እኔም አራስነቴን ሳልጨርስ የመጣሁት እኛ ያላየነውን ልጆቻችን እንዲያዩ በመሻት ነው” ይላሉ።

ቀጥለውም “ለምክክሩ ተወክዬ ሾለ ሀገር ለመመካከር ጥሪው እንደደረሰኝ ያለምንም ማመንታት ሕፃን ልጄን ይዤ ተገኝቻለሁ፣ እኛን የናፈቀንን ሰላም ተመካክረን ልጆቻችን በሰላም እንዲኖሩ የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ በሚል መጥቻለሁ” በማለት ለምክክሩ ያላቸውን ቁርጠኝነት እና ተስፋ ይገልጻሉ።

ሌላኛዋ ጨቅላ ሕፃን ልጃቸውን ይዘው በጉባኤው የተገኙት እናት እንደሚሉት ​“እኛ ባለፍንበት መከራ ልጆቻችን ማለፍ የለባቸውም፤ ልጆቻችን ሰላም ይፈልጋሉ። ያለፈውን ቁርሾ እና ጥላቻ ትተን፣ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን አብሮነታችንን አጠናክረን ሰላምን እናስፍን” ብለዋል።

እናቶች የአራስነት ድካም ሳይበግራቸው በጉባኤው የተገኙትም ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በመሻት መኾኑን ይናገራሉ። ሀገራዊ ምክክሩ መፍትሄ ይዞ እንደሚመጣም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

​✍️ የምክክሩ ፋይዳ ለዘላቂ ሰላም🕊️

​የእነዚህ እናቶች ምስክርነት በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ያለውን የሕዝብ ትልቅ ተስፋ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ሰላም የሚመጣው ከጠመንጃ አፈሙዝ ሳይኾን ከልብ በሚፈልቅ ውይይት መኾኑን እናቶች በተግባር አሳይተዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንዳሉት ጉባኤው እርስ በእርስ በመደማመጥ፣ የታሪክ ጠባሳዎች እንዲሽሩ በማድረግ የወደፊት ዕጣ ፈንታን በጋራ ለመወሰን ትልቅ ዕድል የሚፈጥር “የሀገር ፈውስ” እንደሚኾን ገልጸዋል።

​🙏ሀገራዊ ምክክሩ ውስጣዊ ችግሮች እንዲፈቱ፣ መተማመን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲገነባ መሠረት የሚጥል፣ ለቀጣዩ ትውልድ የሚሰጥ ትልቅ ስጦታ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።

የሁሉንም ወገን ድምጽ በማስተናገድ ለዘላቂ ሰላም እና ለጠንካራ ሀገር ግንባታ መፍትሔ ይዞ እንደሚመጣም ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል።

💭እርስዎስ የእነዚህ እናቶች ጽናት እና የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ምን ተስፋ ሰጥቶዎታል? በሀሳብ መስጫው ያለወትን ሀሳብ ያጋሩን።👇

#አሚኮ #Ethiopia #NationalDialogue

#ባሕር_ዳር፡ሐምሌ11/2018 ዓ.ም

✍️በአሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🧵🤝🏾 የገናናዋ ኢትዮጵያ ንጋት ማብሰሪያ🌅🇪🇹
Next articleየትግራይ ወጣቶችን ለጦርነት የሚሸጠው ሕገ-ወጡ የሕወሃት የጥፋት ቡድን።