🧵🤝🏾 የገናናዋ ኢትዮጵያ ንጋት ማብሰሪያ🌅🇪🇹

40

 

ኢትዮጵያ አስፈሪው እና ሉዓላዊነቷን ያላስደፈረው የጥንት ገናና ታሪኳን ይዛ ከጫፍ እስከ ጫፍ ልጆቿን በአንድ ጣሪያ ሥር ሠበሠበች። ልዩነት የመለያያ አጥር መኾኑ አብቅቶ የመከባበር እና የመዋደድ ድልድይ ኾኗል። በአዲስ ኮንቬንሽን ማዕከል ባሕልን በሚያንጸባርቁ እና በቀለማት ባሸበረቁ አልባሳቶቻቸው ደምቀው፣ በተለያዩ ልሳናት ሲነጋገሩ፣ ኢትዮጵያዊነት የሚለው የጋራ የልብ ቋንቋ አግባብቷቸዋል።

4ሺህ የሀገር ወኪሎች ታላቋን ሀገር ከፍ ለማድረግ ታጥቀው ተነስተዋል። አርሶ አደሮች የልፋት እና የላብ ወራቱ፣ የክረምቱ መግባት አታልሏቸው የሀገር እና የሰላም ጉዳይ ነገ ይደርሳል አላሉም። “ሰላም ከሌለ ምርትም፣ ገበያም፣ ልጅ ማስተማር፣ በነጻነት ወጥቶ መግባትም የለም” በሚል ብሩህ እሳቤ ማረሻቸውን ለጊዜው አሳርፈው የክረምት ሥራው አደራ ይዘውላቸው በሄዱት ወገኖቻቸው እንደሚቀጥል አምነው የሰላምን ዘር ሊዘሩ ወደ አዲስ አበባ ተመሙ።

ወኪሎቹ አጀንዳቸውን አቅፈው ወደ አዳራሹ ሲገቡ፣ እናት ኢትዮጵያ በመንፈስ እጆቿን ዘርግታ ተቀበለቻቸው። “በእኔ ላይ ክፉ አይንካችሁ፤ ያሰባችሁት የአንድነት ሀሳብ ይስመርላችሁ። የእናንተ ልዩነት እና አለመግባባት አስከፍቶኝ በልጆቼ ስረገም እንዳልኖር፣ በነጻነት ተነጋገሩልኝ” ስትል በምሬት እና በተስፋ መሀል ኾና አደራዋን ሰጠች። ወኪሎቹም ፈገግታ በፊታቸው ደምቆ፣ ትልቅ የአንድነት ተስፋን ሰንቀው፣ ኅብረ ብሔራዊነትን በተላበሰ ሞገስ ታጅበው አለፉ።

“ልዩነት በአንድነት ውበት ነው” የሚለው ሀገረኛው አባባል በአዲስ ኮንቬንሽን ማዕከል በተግባር ተገለጠ። ቋንቋ፣ እምነት እና ቀለም በአንድነት የፍቅር ቋት ውስጥ ተደመሩ።

መድረኩ ክቡር በኾነው የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ሲከፈት የሀገር ፍቅር ስሜት በየልቦናው አስተጋባ። የሃይማኖት አባቶች ወደ መድረኩ ወጥተው ፈጣሪ ለታጣው ሰላም ፈጥኖ ምላሽ እንዲሰጥ ጸሎት እና ቡራኬ አደረሱ፤ ሕዝቡ ሁሉ ቆሞ አሜን አለ። “ከዚህ በኋላ የፈተና ዘመን አብቅቶ፣ ሀገራችን የልማት ትኾን ዘንድ በመደማመጥ ተነጋገሩ” ብለው መረቁ።

“ታሪክ ልንሠራ ነው” በሚል ርዕስ የቀረበው ሙዚቃዊ ተውኔትም ልዩነትን አስወግዶ ወደ አንድነት መምጣትን፣ “ወንድሜ እና እህቴ” እየተባባሉ ሀገር ማሻገርን በሚያወሳው ኀያል ዜማው አዳራሹን በአንድ ልብ አናወጠው።

ከደቡብ ኦሞ ዞን ሀመር ወረዳ ካራ ብሔረሰብ የመጡት የምክክሩ ተሳታፊ ሙዶ አኮ “እሳት ቤት መሥራት ቢችል ኖሮ ኢትዮጵያ ከዘመናት በፊት በተሠራች ነበር። ነገር ግን ቤት የሚሠራው እጆች ሲተባበሩ እና ልቦች በእውነት እርስ በርስ ሲደማመጡ ብቻ ነው” በማለት የምክክርን አስፈላጊነት ተናግረዋል።

መሪዎች የሀገር ሕልውና መቀጠል ምስጢሩ የሕዝብ ሀሳብ መኾኑን አረጋግጠዋል። ወኪሎች ምንም ሳይፈሩ የሕዝባቸውን አደራ እንዲወጡ፣ የነገዋን ገናና ኢትዮጵያ ከአዕምሯቸው ስለው በድፍረት እንዲነጋገሩ ጥሪ አቀረቡ። የተሠበሠበውም ሕዝብ የናፈቀው አንድነት እውን እንዲኾን በሞቀ ጭብጨባ አጸደቀ።

የአፍሪካ ኅብረት፣ የኢጋድ እና የሌሎች ሀገራት ተወካዮችም ለአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት የኾነችው ኢትዮጵያ ዳግም ገናናነቷን ልታረጋግጥ የጀመረችውን የምክክር ጉዞ በአክብሮት ታዘቡ። ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በሽምግልና እና በመመካከር የሚፈቱበትን ታላቅ የጥንት እሴት አወደሱ። የዚህ ምክክር ስኬት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካ እና ለዓለም ዳግም ድል መኾኑን መሰከሩ።

አዎ! ጊዜው የሰላም ነው፤ ዛሬ የአንድነት፤ ነገ ደግሞ የገናናዋ ኢትዮጵያ!

ሀገርን በዕውነት የሚወድ ለመነጋገር እና ለመደማመጥ ጆሮውን አይነፍግም፤ ምክክርን የሚነቅፍ እና ከውይይት የሚሸሽ ግን በደም መኖርን የመረጠ ብቻ ነው።

#አሚኮ #NationalDialogue

#አዲስ_አበባ፡ ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም

በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“በሐረሪ ክልል የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክት በራስ አቅም ለመገንባት ይሠራል” ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ
Next article👩‍👧‍👦🕊️አራስነት ያልገደበው የእናቶች የሰላም መሻት፣በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ