
የሰሜን ጎጃም ዞን ” ከተረጅነት ወደ ምርታማነት” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ አሥተዳደር በወንጀጣ ቀበሌ በወል መሬት ላይ የስንዴ ዘር መርሐግብር አከናውኗል።
የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ አሥተዳዳሪ ተመስገን ደግአረገ በዕለቱ 15 ሄክታር የሚደርስ ማሳ በስንዴ ዘር የመሸፈን ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።
በወረዳው ተረጅ እንዳይኖር ኹሉም ራሱን እንዲችል እና በልቶ እንዲያድር ግብዓቶችን በማሟላት የተሻለ ለማምረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ በለጠ ጥጋቡ በምርት ዘመኑ ከ330 በላይ ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን በዞኑ የሚገኙ 27 ሺህ የሚደርሱ ተፈናቃዮችን በራስ አቅም ለመመገብ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። እስካሁንም 18 ሄክታር በዘር ተሸፍኗል ነው ያሉት።
“ከተረጅነት ወደ ምርታማነት” በሚል የሚከናወነው የስንዴ ሰብል ዘር በዞኑ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ራሳቸውን ለማስቻል የሚከናወን ተግባር መኾኑን አንስተዋል።
ዞኑ ያለውን ሰፊ መሬት እና እምቅ የማምረት አቅም በመጠቀም ሙሉ በሙሉ ከእርዳታ ለመላቀቅ የምርት ዘመኑ ወሳኝ ጊዜ ነው ብለዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን የሰው ልጅ በተለያዬ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ከነበረበት ሊፈናቀል እና ሊጎዳ ይችላል ብለዋል።
በዞኑ በተለያዬ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች እንደሚገኙ የገለጹት አሥተዳዳሪው እነዚህ ተፈናቃዮች ተረጅ መኾን እና በድህነት መኖር የለባቸውም ነው ያሉት።
ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ሲባልም እንደ ዞን መልማት እና ምርት መስጠት የሚችልን ጾም የሚያድር መሬት ተጠቅሞ የተጎዱ እና የተፈናቀሉ ሰዎችን ማገዝ እና ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ መቻል ነው ብለዋል።
መተባበር እና መተጋገዝ ከተቻለ ወደፊት ተረጅ ማኅበረሰብ እንዳይኖር ማድረግ እንደሚቻልም አስገንዝበዋል። ከማኅበረሰቡ ገንዘብ በማሠባሠብ፣ ትርፍ በማምረት እና በተለያዩ አግባቦች ራሳቸውን እንዲችሉ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ተረጅነት አዋራጅ ልምምድ ነው ያሉት አሥተዳዳሪው ማኅበረሰቡ እርዳታ መጠበቅን ማቆም አለበት ብለዋል። በየአካባቢው የሚገኙ ሰፊ ጾም የሚያድሩ መሬቶችን አሟጦ በማረስ ምርታማነትን ማሳደግ እና በምግብ ራስን መቻል እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 9/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ- አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
