በምዕራብ ጎጃም ዞን የተሰማራው የዞብል ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ጀማል አማን፤ ሠራዊቱ ፅንፈኛውን ከማፅዳት ጎን ለጎን በቋሪት እና እሁዲት አካባቢ ለቤተክርስቲያን ማሰሪያ ሰባ ሺህ ብር፣ ባለቤቷ በጀግንነት ለተሰዋባት የወታደር ሚስት 197 ሺህ ብር እንዲሁም ንብረቷ በእሳት ለተቃጠለባት እናት 56 ሺህ ብር እገዛ ማድረጉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ማኅበረሰቡ የሚገለገልበትን መንገድ በመጠገን በጎርፍ ምክንያት ከሥራ ውጭ እንዳይኾን ማድረግ መቻሉን ገልጸው መሰል የበጎ አድራጎት ሥራዎች ወደፊትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
የመንገድ ጥገናውን ያከናወነው ሬጅመንት አዛዥ ሻምበል መካሻ አሰፋ በበኩላቸው፣ የሠራዊቱ የበጎ አድራጎት ተግባር የተቀረጸበት እሴት ውጤት መሆኑን አስገንዝበው፣ ክፍሉ እንዲህ አይነት የድጋፍ ተግባራትን ሲያከናውን የሀሳቡ አመንጭ እራሱ አባሉ መሆኑ ሠራዊቱ ምን ያክል የሕዝባዊነት ባለቤት መሆኑን የሚያሳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የገንዘብ ድጋፍ የተደረገላቸው ወይዘሮ አበባ መልኬ እንዳሉት ባለቤታቸው የሰራዊት አባል የነበረ መሆኑንና በጀግንነት እንደተሰዋ አስታውሰው እሱ በህይወት ባይኖርም የክፍሉ የሠራዊት አባላት ከሌላቸው ላይ ቀንሰው የገንዘብ እገዛ ማድረጋቸው ልዩ ስሜት ፈጥሮብኛል ብለዋል።
አዲስ የሚሰራው ቤተክርስቲያን እና የተጠገነው መንገድ ተጠቃሚ የማኅበረሰብ ክፍሎችም በሰጡት አስተያየት ሠራዊቱ በእንደዚህ አይነት የድጋፍ እና የልማት ተግባር ተሳታፊ መሆኑ የነበራቸውን ግንዛቤ በበጎ የቀየረ መሆኑን አንስተው ስለተበረከተላቸው የገንዘብ እና የጉልበት እገዛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዘገባው የምስራቅ ዕዝ ነዉ
