🇪🇹 “ልዩነት ውስጥ ያለ ውበት፤ በውይይት የታጀበ የፖለቲካ ባሕል ለነገዋ ኢትዮጵያ”

3

ኢትዮጵያ ታሪካዊውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ እያካሄደች ነው። በሀገሪቱ ታሪክ የቆዩ እና ሥር የሰደዱ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ግብ ተይዞ ምክክር እየተደረገ ነው።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ያየው ገነት በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የኢትዮጵያን የዘመናት እሴቶች እና ብዝኃነት ከጫፍ እስከ ጫፍ ያቀፈ ታሪካዊ ክስተት እንደኾነ ገልጸዋል።

ጉባኤው የኢትዮጵያን ኅብረ-ብሔራዊ ውበት እና ተፈጥሯዊ ልዩነቶችን እንደ ስጋት ሳይኾን እንደ ሀገር በረከት እና ጸጋ የሚያዩበት አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ መኾኑንም አንስተዋል።

ሂደቱ በሀገሪቱ ትልቅ የታሪክ ክስተት በመኾኑ የሠለጠነ የፖለቲካ ባሕል ማሳያ ነው ብለዋል።

ባለፉት ጊዜያት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምሕዳር በኃይል እና በአንድ አይነት አስተሳሰብ የታጠሩ ቡድኖች ብቻ የሚሰበሰቡበት እንደነበር ያስታወሱት መምህሩ ጉባኤው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማቀናጀቱ ተስፋ ሰጪ መኾኑንም ተናግረዋል። ይህ የጋራ ተሳትፎ ሀገሪቱ ለረጅም ዘመን ያላጣጣመችውን የንግግር የፖለቲካ ባሕል ለማዳበር ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል። 🤝🕊️

አሁን የተጀመረው ሂደት የጸና ሰላም እና አንድነትን ለመገንባት መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።

​የልዩነት ሀሳቦችን በሠለጠነ መንገድ ማስተናገድ ለነገዋ ኢትዮጵያ የጋራ መፍትሔ መሠረት እንደሚጥል ገልጸዋል። የሀሳብ ልዩነትን እንደ ስጋት ሳይሆን እንደ ሀገር ሀብት እና ፀጋ ማየት ይገባል ነው ያሉት።

​”እኔ የሌሎች መፍትሔ ነኝ፤ ሌሎችም የእኔ መፍትሔ ናቸው” የሚል ስሜት በማዳበር የጋራ መፍትሔ መዘየድ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

በዚህም እርስ በርስ በመደማመጥ ለቀጣዩ ትውልድ ጽኑ የኾነች እና የጋራ ማንነት ያላት ሀገር መገንባት ይገባል ብለዋል። 🤝🕊️

​በጉባኤው “እውነተኛ ጆሮ ያስፈልጋል” ያሉት መምህሩ ሁሉም አካላት ሀሳባቸውን በማዋጣት እና በመደማመጥ ወደ ተሻለ የጋራ ግብ መድረስ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ይህ ሂደት ለኢትዮጵያ ትልቅ የታሪክ አሻራ ኾኖ ወደተሻለ ከፍታ እንደሚያሻግራት ገልጸዋል።
​
#አሚኮ #ሀገራዊምክክር #ኢትዮጵያ🇪🇹 #ባሕር_ዳር #ሐምሌ_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየምሥራቅ ዕዝ አንድ ክፍለ ጦር በቋሪት እና እሁዲት አካባቢ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የገንዘብ ድጋፍ እና የመንገድ ጥገና አከናወነ።
Next articleየኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የላቀ አገልግሎት እንዲሰጥ መሥራት ይገባል።