ማን ያሸንፋል ብለን አንጠይቅ፤ 🇪🇹ኢትዮጵያን አሸናፊ እናድርግ!

3
ታሪክ በሌላኛው ምዕራፍ ራሱን ደግሟል። ኢትዮጵያውያን ከውጭ የመጣ ጠላትን ለማባረር፤ የሀገራቸውን ዳር ድንበር እና ሉዓላዊነታቸውን ለማስጠበቅ በአንድነት ተሰልፈው ነበር የዓድዋ ድልን የተጎናጽፉት። ያኔ ብሔር፣ ሃይማኖት ሳይሉ ነበር በአንድነት የተዋደቁት።
ታዲያ ዛሬ ታሪክ ራሱን በሌላ ገጽታ ደግሟል። በፊት ጠላትን ለማባረር በቅንጅት የዘመቱ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ደግሞ ችግሮቻቸውን በውይይት ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር🤝 ላይ ተቀምጠዋል። የፈተናቸው የውስጥ ችግር በውይይት ለመፍታት፤ ልዩነታቸውን በአንድነት ለማሠር፤ ብዝኃነታቸውን በውበት ለመግለጽ በአንድ አዳራሽ ተሠባሥበዋል።
ይህ መሠባሠባቸው ደግሞ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ አብሮነትን፣ መቻቻልን፣ የፖለቲካ እሴትን፣ የኢኮኖሚ እምርታን እንደሚፈጥርላቸው አምነዋል።
ለቀጣዩ ትውልድ የተሰናሰለች፤ በልዩነት ውስጥ አንድነትን የገነባች፤ በብዝኃነት ውስጥ እኩልነትን ያጸናች፤ ችግርን በጽናት በውይይት ማለፍ እንደሚቻል የምታሳይ ሀገርን ለማስተላለፍ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው አምነው ወደ ተግባር ገብተዋል።
🤝 የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያውያን የወደፊት መጻኢ ተስፋቸውን የሚወስኑበት፤ ሀገራዊ መግባባት ላይ የሚደርሱበት፤ ችግሮችን በውይይት የምትፈታ ሀገር የሚገነቡበት እና ዳግም ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚኾኑበት እንደሚኾንም ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮምሽን ከአራት ዓመታት ብርቱ ሥራ በኋላ የምክክር ጉባኤውን ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም አስጀምሯል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኦሞ ዞን የሐመር ወረዳ የካራ ማኅበረሰብ ተወካይ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተሳታፊ ሙዶ አኮ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ምክንያት ልባቸው በተስፋ መሞላቱን ገልጸዋል።
ለብዙ ዘመናት ሌሎች ሲናገሩ እና ሲወስኑ እኛ ሴቶች ግን ታሪክን ከሩቅ እንመለከት ነበር ነው ያሉት። ዛሬ ሀገራዊ ምክክሩ የኔ ድምጽ ብቻ አይደለም ያሉት ሙዶ አኮ የብዙ ኢትዮጵያውያን ድምጽ መኾኑን ተናግረዋል። ባለመነጋገራችን ብዙ ነገር አጥተናል እንባ ጥላቻ እና ሀዘንን አትርፈናል ነው ያሉት።
ቤት የሚገነባው እጆች ሲተባበሩ እና ልቦች ሲደማመጡ መኾኑን አንስተዋል። ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት፤ ተመካክረን ችግሮቻችንን እንፍታ፤ ማን ያሸንፋል ብለን አንጠይቅ ኢትዮጵያን አሸናፊ እናድርግ ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
🇪🇹 የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ በምክክሩ የሀገርን እጣ ፈንታ የሚወስኑ፤ በመሠረታዊ የሀገር ግንባታ ጉዳዮች ላይ መግባባት የሚፈጥሩ፤ ለዘመናት ሲያጋጩ የነበሩ ጉዳዮች ላይ የጋራ መፍትሔ በማስቀመጥ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ማስፈን ይጠበቃል ነው ያሉት። ታላቋን ኢትዮጵያ ማዕከል ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ጉባኤው የሀገርን የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ግንኙነት አቅጣጫ የሚያቀና፤ ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ እና አስተማማኝ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ብለዋል።
የናይጄሪያው የቀድሞው ፕሬዝዳንት እና በአፍሪካ ኅብረት የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ሀገራዊ ምክክር ኮምሽኑ ለኢትዮጵያ እና በጠቅላላው ለአፍሪካዊያን ታሪካዊ መኾኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እየሠራችው ባለችው ተግባር ጥንካሬን እና ዕድልን መመልከታቸውንም ገልጸዋል። ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከልባቸው እንዲመክሩም አሳስበዋል።
በያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሐረር ከተማ የኮሪደር ልማት፤ የመሠረተ ልማት ሽግግር እና የወደፊት ተስፋ
Next articleጾም የሚያድሩ መሬቶችን አሟጦ በማረስ ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል።