
የኮሪደር ልማቱ ሐረር ከተማ ለረዥም ዓመታት ከነበረችበት የቁልቁልት ጉዞ ተላቃ የማንሰራራት ጉዞ እንድትጀምር የታሪክ እጥፋት የፈጠረ መኾኑን የሀረሪ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ አስታውቀዋል።
የሀረሪ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።
በጉባኤ ላይም የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ የ2018 የበጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ ባቀረቡት ሪፖርትም በተለይም በክልሉ ለሌሎችም ተሞክሮ መኾን የቻለ ስኬታማ የኮሪደር ልማት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።
በኮሪደር ልማት ሥራዎቹም ነባራዊ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ የአካባቢውን ጸጋን በመጠቀም እና በፈጠራ እና ፍጥነት በመታገዝ እንዲሁም በዝቅተኛ ወጪ የተከናወኑ እንደኾኑ ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራዎቹም ከተማውን ጽዱ፤ ውብ እና ማራኪ በማድረግ ሐረር ከተማ ለነዋሪው እና ለጎብኝዎች ምቹ እንድትኾን ከፍተኛ እርብርብ መደረጉን አንስተዋል።
በ2018 በጀት ዓመት 5 የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የተናገሩት ርእሰ መስተዳድሩ ሌሎች 5 የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶችም በሂደት ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
በከተማው የተሠሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎችም የአስፋልት እና የብስክሌት መንገዶች፤ የእግረኛ መንገድ፤ የመንገድ ዳር መብራት እንዲሁም የአረንጓዴ ስፍራን ያካተተ መኾኑን ተናግረዋል።
በተከናወነው የኮሪደር ልማት ሥራውም በርካታ ሴቶች እና ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረጉን ነው የገለጹት።
ቅንጅታዊ አሠራርን በተግባር እውን ማድረግ መቻሉም ለሥራው ውጤታሚነት ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን ጠቅሰው በክልላችን ለመጀመሪያ ጊዜ የኤሌክትሪክ፣ የውኃ እና የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች በመሬት ውስጥ ለውስጥ እንዲዘረጋ የማድረግ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራዎች አማካኝነት ሐረር ከተማ ለረዥም ዓመታት ከነበረችበት የቁልቁልት ጉዞ ተላቅቃ ወደ የማንሰራራት ጉዞ እንድትጀምር እና የታሪክ እጥፋት የፈጠረ መኾኑን ነው ርእሰ መሥተዳድሩ የተናገሩት።
ይህም በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተስፋ እና ቅቡልነትን በመፍጠር በከተማው እድገት የማይፋቅ አሻራ አሳርፏል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
