🌅 ዛሬ በኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ይከፈታል! አሮጌው ምእራፍ ይዘጋል! 🤝

3

 

ኢትዮጵያውያን በአንድነት መምከርን ያውቁበታል፤ እርቅ፣ ስምምነት እና አብሮነትን ማስቀጠል መገለጫቸው ነው፤ በዘመናት ቆይታቸው እንደ ባሕላቸው፣ እንደ ቋንቋቸው የዳኝነት ሥርዓትን ዘርግተው ለዘመናት ተገልግለውበታል።

ያጠፋ የሚቀጣበት፤ የበደለ የሚክስበት፤ ይቅርታ እና መቻቻል የሚነግሥበት፤ መደማመጥ የጸናበት፤ ፍቅር እና አብሮነት የጎላበት ድንቅ የውይይት ማኅበራዊ እሴቶች ባለቤት ናት ኢትዮጵያ።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ሽምግልና (ሸንጎ)፣ አበጋር፣ ጃርሱማ፣ ገዳ፣ ጆካ፣ ቂጫ፣ አፊኒ፣ ኦገት፣ ባይቶ፣ ማክአባን፣ ሄር፣ ኢናሽማ እና ሌሎችም የችግር መፍቻ የውይይት የሽምግልና ሥርዓቶች አሉ።

ይህ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓታቸውም ለዘመናት በአንድነት እንዲኖሩ፤ ችግሮችን በውይይት እንዲፈቱ፤ የሀገርን ዳር ድንበር በአንድነት እንዲጠብቁ፤ ሉዓላዊነታቸውን አጽንተው እንዲዘልቁ አሥችሏቸዋል።

🤝 ዛሬስ

የገጠማቸውን ፈተና፤ የታሪክ እጥፋትን፤ የብሔር ተኮር ግጭትን፤ መከፋፈልን ታሪክ አድርጎ ለማስቀረት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁመው አጀንዳዎችን ለይተዋል። አጀንዳ መለየት ብቻም ሳይኾን ሐምሌ 8/2018ዓ.ም በአንድነት ሊመክሩ፤ መከፋፈልን ሊያሥቀሩ፤ ዘረኝነትን ሊያጠፉ ቀጠሮ ይዘዋል።

🤝✍️ ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም ለኢትዮጵያውያን

ሐምሌ 8 ለኢትዮጵያውያን ተስፋ ሰንቋል፤ እግሮች ሁሉ ወደ ምክክር አምርተዋል፤ የኔ ብቻ ቀርቶ እኛነትን ለማራመድ ቆርጠዋል፤ በተስፋዋ ምድር ብርሃንን ሊተክሉ እጆች ሁሉ ለውይይት ተዘርግተዋል።

ዛሬ የኢትዮጵያውያን ቀን ነው፤ ለዘመናት ተብትቦ የያዛቸውን የመከፋፈል ሠንሠለት የሚበጥሱበት፤ አብሮነታቸው አንድነታቸውን በማይፈርስ ጽኑ አለት የሚያንጹበት ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ በምክክር ጉባኤው ለሚሳተፉ አካላት በሰጡት ማብራሪያ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የዓድዋን መንፈስ በመሰነቅ ለሀገር ግንባታ ያዳበርነውን ተግባር ወደ ምክክር እና መግባባት መቀየር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ምክክሩ ለኢትዮጵያ መጻኢ ዕድል የሚደረግ ውይይት መኾኑንም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 4 ሺህ ሰዎች ስለ ሀገራቸው፣ ስለ ሰላም፣ ስለ ሀገር ግንባታ እና ስለ ሰብዓዊ መብት የሚመክሩበት ጊዜ ነው ብለዋል።

ጠንካራ ባሕላዊ እሴቶችን ከዘመናዊ አካሄድ ጋር በትክክል ማሥተሳሰር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የዛሬውን ሀገራዊ ምክክር አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ይህ መድረክ ፍቱን የፖለቲካ መድረክ ብቻ ሳይኾን የመጭውን ትውልድ ዕጣ ፈንታ እና የወደፊት ተስፋ የሚወስን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መኾኑን ገልጸዋል።

ሀገር የምትሻው የጠመንጃ ኀይልን ሳይኾን በሀሳብ ብስለት፣ በዕውነት፣ በዕውቀት እና በጽናት ታጥቀው የተሰናዱ የሰላም ታጋዮችን እንደኾነም ጠቁመዋል።

“ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋት እና ሁለንተናዊ ብልጽግና የምትተጉ፣ የኢትዮጵያ ታላቅነት ግድ የሚላችሁ ሁሉ በምክክር መድረኩ ላይ በንቃት እንድትሳተፉ” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

እርስዎ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ ታላቅነት ምን ለማበርከት አቅደዋል? ሃሳብዎን በሃሳብ መስጫ ሳጥኑ ውስጥ ያጋሩን? 👇👇👇

#አሚኮ_ዜና#ሀገራዊ_ምክክር #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹#AmecoNews #National_Dialogue #Amhara_Region #Ethiopia 🇪🇹

#ባሕር_ዳር_ሐምሌ_8_2018_ዓ_ም

በያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ሰማይ ቢቀደድ ሽማግሌ ይሰፋዋል ይሉ ዘንድ”
Next articleየንጋት ጮራ – የኢትዮጵያ የልብ መሻት በምክክር አዳራሽ ውስጥ