የንጋት ጮራ – የኢትዮጵያ የልብ መሻት በምክክር አዳራሽ ውስጥ

4
🌟
🌟
ዛሬ ኢትዮጵያ የእናትነት የፍቅር እጆቿን ለልጆቿ ዘርግታለች። የ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ወኪል ልጆቿን በአንድ ጣሪያ ሥር በልዩ ፍቅር አሰባስባለች። ብሔር፣ ሃይማኖት እና የቆዳ ቀለም ግርዶሽ አልኾኑም፤ ድንበሮችም ማንነትን አልከፋፈሉም። ሁሉም በኢትዮጵያዊነት ክር ተጋምደዋል። የሰላም እና የአንድነትን ዜማ ለመዘመር በአንድ ታላቅ አዳራሽ ከትመዋል።
ለዘመናት አብሮነታችንን የፈተኑ ቁስሎች አሉ። ወንድምን ከወንድም ያራራቁ ታሪካዊ ስብራቶችም ነበሩ። የዛሬው ዕለት ግን እነዚህን ደዌዎች ለመደበቅ አልተዘጋጀም። ይልቁንም አውጥቶ በማከም ከሥሩ ለመንቀል ያለመ ነው። ይህ በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተዘረጋ ታሪካዊ መድረክ ነው። መድረኩ የወቀሳ ሳይኾን የፈውስ ጠረጴዛ ነው፤ የክስ ሳይኾን የካሳ እና የዕርቅ አውድማ ነው።
በዚህ አዳራሽ ውስጥ የልብ ትርታ በግልጽ ይሰማል። አንዱ የሌላውን ህመም ከልብ ያዳምጣል። ሁሉም ለነገዋ ሀገር ራዕይ በጋራ ይሳላል። ይህ መድረክ የልዩነት ማጥፊያ አይደለም። ይልቁንም ልዩነቶች እንደ ኅብረ-ቀለም የሚያሸበርቁበት የጋራ ሸራ ነው። እውነተኛ ይቅርታ ከልብ ይመነጫል። በጥርጣሬ የተገነቡ ግድግዳዎችም ይፈርሳሉ። በመከባበር ላይ የተመሠረተ ጽኑ ድልድይ ይገነባል።
የዚህ ታላቅ ምክክር ግብ ግልጽ እና ማራኪ ነው። ማንም ዜጋ በየትኛውም የሀገሪቱ ማዕዘን በነጻነት ይኖራል። ያለ አንዳች ስጋት ይዘዋወራል፤ ይሠራል፣ ሀብትም ያፈራል። ቋንቋውን እና ማንነቱን አክብሮ ከሌላው ወገኑ ጋር በፍቅር ይቆራኛል።
ዛሬ በአንድ አዳራሽ የተጀመረው ይህ የልብ ውይይት ትልቅ ተስፋ ነው። ነገ በየቤቱ እና በየመንደሩ የሚቀጥል የሰላም ንቅናቄ ይኾናል። ከዚህ የምክክር ማሕጸን አዲስ እና ጠንካራ ሀገር ዳግም ትወለዳለች። የጥላቻ ትርክት በፍቅር ዜማ የሚተካበት ብሩህ ንጋትም ይፈነጥቃል።
“በምክክር የታነጸ ዳስ የዘመናት ማዕበል አያፈርሰውም፤ ንግግሩ የከሸፈበት እና በእልህ የቆመ ግንብ ግን ነፋስ ሳይነካው በራሱ ይናዳል” የሚል አባባል አለ። ታሪካችን ተመካክረው አንድነታቸውን እንዳዳኑት እንጂ ንግግራቸው ከሽፎ ሀገራቸውን እንዳፈረሱት እንዳይኾን የተጀመረው የምክክር ጠረጴዛ የፈውስ፣ የዕርቅ እና የዘላቂ አንድነት መሠረት እንዲኾን በቁርጠኝነት መሥራት፣ በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋል።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article🌅 ዛሬ በኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ይከፈታል! አሮጌው ምእራፍ ይዘጋል! 🤝
Next articleየመጨረሻ ደቂቃዎች- በኢትዮጵያ የምክክር ብርሃን !