የመጨረሻ ደቂቃዎች- በኢትዮጵያ የምክክር ብርሃን !

5
በኢትዮጵያ የምክክር ብርሃን ፈነጠቀ፤ የማለዳ ጮራን ተመልክተው፤ ውብ ገጽታ ተጎናጽፈው ስለ አብሮነታቸው፤ ስለ እሴቶቻቸው በአንድነት ሊመክሩ የወደፊቷን ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ሊቀርጹ በአንድ ማዕከል ተሠብሥበዋል።
ኢትዮጵያ ሆይ ችግሮችሽ ሊቀረፉ፤ በዘር መከፋፈል ሊወገድ፤ የወደፊት ርዕይሽ ሊቀረጽ፤ የፖለቲካ መሠረትሽ ሊጣል፤ ማኅበራዊ እሴትሽ ሊጎላ ልጆችሽ በአንድ ማማ ሥር ተቀምጠዋል።
ነገሽ በብርሃን ሊሞላ፤ ችግሮችሽ በውይይት ሊፈቱ፤ ሀዘንሽ ሊያከትም፤ ደስታሽ ሊያብብ ልጆችሽ በሀገራዊ ምክክር በአንድነት ተሠብሥበዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮምሽን ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ በበርካታ ከተሞች እና ወረዳዎችን በማካለል፤ ከ200 ሺህ በላይ ዜጎችን ድምጻቸውን እንዲያሰሙ በማድረግ ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአንድነት እንዲሰባሰቡ አድርጓል።
በስምንት አጀንዳዎች ከ4 ሺህ በላይ ዜጎች ከደቂቃዎች በኋላ በአንድነት መምከር ይጀምራሉ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ አርሶ አደሮች፤ የመንግሥት ሠራተኞች፤ የግል ሠራተኞች በአጠቃላይ ሁሉም ማኅበረሰብ ለምክክር የሚያበቁ አጀንዳዎችን አቅርቧል ብለዋል።
የሀገር ውስጥ ብቻ ሳይኾን ከሀገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በምክክር ኮምሽኑ እየተሳተፉ ነው።
4 ሺህ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ፤ ከ150 በላይ አማካሪዎች፤ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎችን በማካተት ይካሄዳል ብለዋል።
“እናንተ በዚህ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ስትመጡ የወከላችሁትን ማኅበረሰብ ድምፅ እና ምኞት ለማስተጋባት ብቻ ሳይኾን ለሀገራችን የጋራ ዕድል እና የወደፊት ዕጣ ፈንታ መሠረት ለመጣል ጭምር በመኾኑ ትከሻችሁ ላይ የወደቀው ኀላፊነት እጅግ ታላቅ እና ጥልቅ ነው” ብለዋል።
መልካም ዕድል ለኢትዮጵያችን !
#አሚኮ_ዜና#ሀገራዊምክክር #ኢትዮጵያ
#ባሕርዳር#ሐምሌ_08_2018ዓ.ም
ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
Previous articleየንጋት ጮራ – የኢትዮጵያ የልብ መሻት በምክክር አዳራሽ ውስጥ
Next articleአዲስ ተስፋ ለኢትዮጵያ!