
ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ፣ የተለያየ ባሕል እና በርካታ እሴቶች ያሏት ታላቅ ሀገር ናት። ይሄን ታላቅነቷን አፅንቶ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ታሪካዊ ልዩነቶች በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መምከር በጣም አስፈላጊ ነው።
ዛሬ የሚጀምረው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤም ሀገሪቱ ካጋጠሟት ውስብስብ ችግሮች ወጥታ ወደ ተሻለ ጎዳና እንድታመራ ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ተስፋ የጣሉበት ነው።
ጉባኤው ለኢትዮጵያዊያን አዲስ ተስፋን የፈጠረ የመሆኑ ምክንያትም፦
በቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት መፍጠር፦
ስለ ሀገር ግንባታ፣ ስለ መፃኢው የሀገሪቱ አቅጣጫ የሚነሱ የሃሳብ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የምክክር መድረኩ ወሳኝ ነው። ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ ውይይት የጋራ መግባባትን ያመጣልና።
የጠመንጃ ድምፅን በሃሳብ የበላይነት መተካት፦
የፖለቲካ ልዩነቶች በጦርነት እና በኃይል ለመፍታት የተደረጉ ሙከራዎች የሕይወት እና የንብረት ውድመት ከማስከተል ባለፈ ዘላቂ መፍትሄ አላመጡም። ሀገራዊ ምክክሩ “ከኃይል አማራጭ ይልቅ የሃሳብ የበላይነት” እንዲነግስ ያደርጋል።
ከልሂቃን፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሴቶች እና ወጣቶች እስከ ማኅበረሰብ ድረስ ሁሉም ድምፃቸው የሚያሰሙበት ዕድል መፈጠሩ የውይይቱን ውጤት በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ያደርገዋል።
የእኛ ሚና ምንድነው?
የሀገራዊ ምክክሩ ዋነኛ ባለቤቶች ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ናቸው። የሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የኮሚሽኑ ወይም የፖለቲከኞች ብቻ ኃላፊነት አይደለም። እያንዳንዱ ዜጋ ሂደቱን በቅንነት መደገፍ፣ ሃሳብን በሰላማዊ መንገድ ማንሸራሸር እና ሌላውን ለመስማት ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል።
ሀገራዊ ምክክሩ ለልጆቻችን የምናስተላልፋትን ሰላማዊት እና የበለፀገች ኢትዮጵያ ለመገንባት የምንጠቀምበት ወርቃማ ዕድላችን ነውና ይህንን እድል በአግባቡ መጠቀም ይጠበቃል።
#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 08/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
