
ኢትዮጵያ በረጅም የታሪክ ዘመኗ ያልተፈራረቀባት የጦርነት ዘመቻ፣ ያላንዣበበባት የጥፋት ደመና፣ ያልተጸነሰባት የፖለቲካ ሴራ፣ ያልተሸረበባት የዲፕሎማሲ ጫና እና ያልጎረፈባት የተንኮል ማዕበል አልነበረም።
ኾኖም ይህች ጥንታዊት፣ ታሪካዊት እና ገናና ሀገር በየጊዜው በጠላቶቿ የሚደቀንባትን የፈተና ማዕበል ሁሉ በብረት አጥርነት የምትሻገር የጽናት ማህተም ኾና ዘልቃለች።
እርሷ በፈተናዎች እቶን ውስጥ አልፋ ይበልጥ የመውጣት ተፈጥሯዊ ጥበብ እና ውስጣዊ ምስጢር አላት። ጠላቶቿን ድል በነሳች ቁጥር እንደ ፀሐይ ታበራለች፣ እንደ ጨረቃ ትደምቃለች፣ እንደ አደይ አበባ ፈክታም ታብባለች። አይበገሬነቷ በፈተናዎች እሳት ውስጥ አልፎ እንደ ከበረ ወርቅ ያበራል።
ዛሬም የትላንት ታሪካዊ ጠላቶቿ የትላንት የበቀል መርዛቸውን ሊረጩባት፣ የጥፋት መረባቸውን ሊዘረጉባት እና የፖለቲካ ሴራቸውን ሊጠመጥሙባት ቀን ከሌት እየታተሩ ይገኛሉ።
የእርሷ ፈተና መቼም አያልቅም፤ ወልዳ ባሳደገችው እና ከጉያዋ በወጣው ከዳተኛ፣ ተላላኪ እና ቅጥረኛ ባንዳ፤ ከባሕር ማዶ በሚጮሁ የቁም እስረኞች እፎይታ አጥታለች።
የኢትዮጵያ ማደግ የሚያማቸው፣ የእርሷ መበልጸግ እረፍት የሚነሳቸው፣ የእርሷ ሰላም ውሎ ማደር የሚያበሳጫቸው፣ የእርሷ የልማት ጉዞ የሚያስቀናቸው፣ የእርሷ የዲፕሎማሲ ስኬት የሚከነክናቸው፣ የእርሷ የቀጣናው ኀያልነት እና የበላይነት የሚያስፈራቸው እና የእርሷ ጀግንነት እና አልደፈርም ባይነት የሚያስበረግጋቸው የጠላት ኀይሎች ሉዓላዊነቷን ሊዳፈሩ ሁልጊዜም ከማለም እና ከመተንኮስ ወደ ኋላ አላሉም።
ታዲያ እነዚህ የጥፋት ኀይሎች ኢትዮጵያን ለማንበርከክ እና ለመጣል ይሞክሩ እንጅ በቁርጥ ቀን ልጆቿ እንደ ብረት የጠነከረ ክንድ ተደቁሰው ተመልሰዋል፤ አትተንኩሷት፤ የነኳት ሁሉ የሽንፈት ካባን ተላብሰዋል፤ የመከራንም ጽዋ ተጎንጭተዋልና።
ምኞታቸው እንደ አቧራ በኗል፤ ዓላማቸው እንደ ጉም ተኗል፤ ተልዕኳቸውም እንደ ሰም ቀልጧል። ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ እና በብሔራዊ ጥቅሟ ላይ ፈጽሞ እንደማትደራደር በተግባር አይተዋል። ይህ የማይናወጠው የጽናት ማህተም በዓለም አቀፍ መድረክ ታትሟል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ እና የቀይ ባሕር የውኃ ሀብቶች የሕልውናዋ እና የብሔራዊ ጥቅሟ ዋነኛ ማዕከል መኾናቸውን በግልጽ አውጃለች።
የውጭ ኀይሎች እነዚህን የተፈጥሮ ፀጋዎች እንደ ማነቆ በመጠቀም ሀገሪቱን በድህነት ገመድ ለመቆለፍ የሚያደርጉት ጥረት መክኗል፤ በኢኮኖሚም ኾነ በጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ሥር ለመጠቅለል ያካሄዱት ውሥብሥብ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እና ወታደራዊ ዘመቻ ሙሉ በሙሉ ከሽፏል።
ለሀገር ሕልውና መከበር ግንባር ቀደም መስዋዕትነት እየከፈለ ያለው የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ባሳየው ወደር የለሽ ጀግንነት እና የደም ዋጋ የሀገርን ሉዓላዊነት ለመዳፈር የመጣውን ጠላት ሁሉ ዛሬም እንደ ትላንቱ ድባቅ እየመታው ይገኛል።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር ብቻ ሳይኾን በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር ቀጣና ያላትን የበላይነት ድርሻ ለማጽናት በቁርጠኝነት እየታተረች መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መግለጻቸው ይታወሳል።
የዛሬው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የዘመናዊ ትጥቅ እና ቴክኖሎጂ ባለቤት መኾኑን የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገልጸዋል።
የምድር፣ የአየር እና የሳይበር የመከላከል አቅሙን በማዘመን የጠላትን እንቅስቃሴ ገና ከሩቅ ማክሸፍ የሚያስችል አቅም መገንባቱንም ጠቅሰዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት በወታደራዊ ሳይንስ፣ በስትራቴጂካዊ አመራር እና በቴክኖሎጂ የሠለጠኑ አባላትን ያቀፈ አስተማማኝ ተቋም ኾኗል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
