
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ42ኛ ጊዜ የሚከበረውን የጡት ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር በደሴ አጠቃላይ ሰፔሻላይዝድ ሆስፒታል አካሂዷል፡፡
ወይዘሮ ሠርኬ ከበደ ከ6 ዓመት በፊት ነበር የሕመም ስሜት በግራ ጡቴ ላይ የተሠማኝ ይላሉ። ያንጊዜ ሁለተኛ ልጃቸውን ነፍሰጡር እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
ወደ ተለያዩ ሆስፒታሎች ለምርመራ በመሄድ የጡት ካንሰር ሕመም እንዳለባቸውም ያረጋግጣሉ። የሕመሙ መከሰት በወቅቱ ቢያስደነግጣቸውም ተገቢውን ሕክምና በማድረጋቸው መዳን ችለዋል።
ተገቢው ሕክምና በትክክለኛው ጊዜ ከተደረገ መዳን እንደሚቻል ያነሱት ወይዘሮ ሠርኬ ማኅበረሰቡ ተገቢውን ምርመራ እና ሕክምና እንዲያደርግ መክረዋል፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና በደሴ አጠቃላይ ሰፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካንሰር ሰፔሻሊስት ዶክተር ያሲን ወርቁ የጡት ካንሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ በስርጭቱ ቀዳሚ መኾኑን አንስተዋል።
በየዓመቱ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች የጡት ካንሰር ታማሚዎች ተለይተው 685 ሺህ የሚኾኑት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ገልጸዋል።
በሆሰፒታሉ ከልየታ እና ምርመራ ባሻገር ተገቢውን ሕክምና እየሰጡ መኾኑን የገለጹት ዶክተር ያሲን ሰዎች ሳይዘናጉ ክትትል እንዲያደረጉም አሳስበዋል።
የደሴ አጠቃላይ ሰፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ ዶክተር ሃይማኖት አየለ አገልገሎት ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉ ለሚያመሩ ዜጎች ሁሉ የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡
አሁን ላይ የጡት ካንሰር ምርመራ የሚያደረጉ ሴቶች ቁጥር ከፍተኛ መኾኑን ነው የጠቆሙት፡፡ ከምርመራ በኋላም አስፈላጊውን ሕክምና እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጿል፡፡ በጥቅምት ወር የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብርን ምክንያት በማድረግ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 የኾኑ ሴቶች ለምርመራ ምንም ዓይነት ክፍያ ሳይጠየቁ ምርመራ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች ባለሙያ እና የካንሰር ፕሮግራም አስተባባ ዶክተር ቴወድሮስ ጌታቸው ማኅበረሰቡ በጡት ካንሰር ዙሪያ ዕውቀት እንዲኖረው እና ወደ ሕክምና ተቋም እንዲመጣ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ወሩ ታስቦ እንዲቆይ እና ግንዛቤው እንዲፈጠር የንቅናቄ ሥራው ወሳኝ ነውም ብለዋል፡፡ በሽታው ከመከሰቱ በፊት ሊወሰዱ ከሚችሉ ቅድመ ጥንቃቄዎች መካከል በየጊዜው ምርመራ ማድረግ፣ በየወሩ ጡታቸውን በአግባቡ በመፈተሽ እብጠት መኖሩን እና አለመኖሩን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።
ከወሊድ በኋላ ጡት ማጥባት፣ የአልኮል መጠጥ መቀነስ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የሆርሞን ሕክምናዎችን ማድረግ እና ለጨረር ተጋላጭነትን መቀነስ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
