በቱሪዝም ሃብት የታደለውን አካባቢ ለማልማት እየተሠራ ነው።

1
ዓለማቀፉ የቱሪዝም ቀን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በተዋበው ስፍራ ጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ተከብሯል። በማዕከላዊ ጎንደር  ዞን ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማልማት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ተገልጿል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ የዞኑን እምቅ የቱሪዝም መዳረሻ ማልማት እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስተዋወቅ ይገባል ብለዋል።
ቱሪዝም ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዘርፍ መኾኑን አብራርተዋል። ዞኑ በቱሪዝም ዘርፍ እምቅ አቅም እንዳለው ተገልጿል። በመዳረሻዎች አካባቢ የሚገነቡ ሆቴሎች፣ የመብራት እና የኔትወርክ መሠረተ ልማቶችን የማልማት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
ጎብኝዎች ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ዞኑን እንዲያውቁ መሥራት ይጠበቃልም ብለዋል። ቅርሶችን ዲጂታል በኾነ መንገድ መመዝገብ እና ለቀጣዩ ትውልድ ማስቀመጥ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በዞኑ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመለየት የማልማት ሥራ እየተሠራ መኾኑን የጠቆሙት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ድግስ መለሰ ቱሪዝም ባሕልን እና ቅርስን ለዓለም ለማስተዋወቅ የጎላ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።
በዞኑ የሚገኙ ነባር ዘጠኝ ቅርሶች ጥገና ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል። የቱሪዝም ዘርፉን ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ማስተዋወቅ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ነው ተብሏል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ጎርጎራ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የበለጠ ተገልጣለች ነው ያሉት። በሰላም እጦቱ ምክንያት የጎብኝዎች ቁጥር መቀነሱም ተነስቷል። ሰላምን ለማረጋገጥ በጋራ መሥራት ይጠበቃልም ብለዋል።
የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል መፍጠሩም ተመላክቷል።
✍️ዘጋቢ፦ ደስታ ካሣ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበሕገ-ወጥ ንግድ ላይ የተወሰደው ጠንካራ እርምጃ
Next articleለጡት ካንሰር በሽታ እንዳይጋለጡ ምን ያክል ክትትል ያደርጋሉ ? የጡት ካንሰር በዓለማችን በብዛት ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች ውስጥ ይመደባል።