በሕገ-ወጥ ንግድ ላይ የተወሰደው ጠንካራ እርምጃ

1
የአማራ ክልል የጸረ-ኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር ጥምር ግብረ-ኃይል የወንጀል ጉዳዮች ቴክኒክ ኮሚቴ የ2019 በጀት ዓመት የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም ኮንትሮባንድ እና ሕገ ወጥ ንግድ የሀገራችንን ኢኮኖሚ የሚፈትኑ፣ የኑሮ ውድነት የሚያባብሱ እና የሕጋዊ ነጋዴዎችን ተጠቃሚነት የሚጻረሩ ወንጀሎች መኾናቸን ገልጸዋል።
ባለፉት ሦስት ወራት በዋና ዋና የንግድ መስመሮች፣ የንግድ ቤቶች እና የድንበር አካባቢዎች በተደረጉ ድንገተኛ ፍተሻዎች እና የክትትል ሥራዎች የተሻለ ውጤት መገኘቱን ነው የተናገሩት። ሕግ ተላልፈው በተገኙ አካላት ላይ የተወሰዱ አሥተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃዎች ለሕገ ወጦች ማስጠንቀቂያ መልዕክት ናቸውም ብለዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ቴክኖሎጂን በመጠቀም፣ ቅልጥፍናን ማሳደግ እና ከኅብረተሰቡ ለሚገኙ ጥቆማዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት ይገባል ነው ያሉት። የጸጥታ፣ የፍትሕ፣ የጉምሩክ እና የንግድ አካላት ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ሕገ-ወጥ ንግድን በጠንካራ አሠራር መከላከል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሒም ሙሐመድ (ዶ.ር) ሕገ ወጥ ንግድን፣ የኮንትሮባንድ ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ ተገቢ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ገልጸዋል። የወጭ እና ገቢ ስትራቴጂክ ምርቶችን ቁጥጥር እና ክትትል ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በቅንጅት መሥራት ይገባል ያሉት ኀላፊው በተለይም የነዳጅ ምርትን በአግባቡ መምራት ይገባል ብለዋል። ተቋማት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር ሙሉጌታ አሻግሬ ቴክኒክ ኮሚቴው በወሰዳቸው አሥተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃዎች በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ ማደረጉን ገልጸዋል።
በሕገ-ወጥ ንግድ በተሰማሩ ከ84 ሺህ በላይ ነጋዴዎች እና የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ላይ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ የማሸግ፣ እቃ የማገድ እና ፍቃድ የመሰረዝን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ነው የተናገሩት።
የምግብ፣ የመድኃኒት እና የውበት እቃዎች ግምታቸው 66 ሚሊዮን በላይ ገንዘብ የሚያወጡ የንግድ እቃዎች እንዲወገዱ መደረጉንም አንስተዋል። በቀጣይም ሕገ-ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ በኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሱትን አደገኛ ተጽዕኖ ለመግታት እስከ ወረዳ ድርስ በቅንጅት ይሠራል ብለዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኢኮኖሚ እና ልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ዋና መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ደጀን ወዳጅ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል የቅድመ መከላከል ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ በቁጥጥር እና በክትትል ሥራው በርካታ ሀብት ማዳን እንደተቻለ ገልጸዋል።
ወንጀል ፈጽመው አድራሻቸውን በሚቀይሩ አካላት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል በቅንጅት ይሠራልም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴ አመራር እና የአባላት ምደባን አጸደቀ።
Next articleበቱሪዝም ሃብት የታደለውን አካባቢ ለማልማት እየተሠራ ነው።