
ረጅም ታሪክ፣ ቱባ ባሕል እና ኅብረ-ብሔራዊነት መለያዋ የኾነችው ኢትዮጵያ የነገ ተስፋዋን አስተማማኝ ለማድረግ አዲስ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል ይበልጥ ብሩህ ለማድረግም ምክክር ቁልፍ እና ታሪካዊ ሚና ይጫወታል።
ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባትም ኢትዮጵያ አሁን ላይ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም እና በመላ ሀገሪቱ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ለመጻኢ ዕጣ ፈንታ በታላቅ ምክክር ላይ ትገኛለች።
ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤም ዛሬ በይፋ ይጀመራል።
መመካከር፣ መወያየት እና መነጋገር ችግሮችን በመፍታት እና የሰላም ተምሳሌት በመኾን በአንድነት ሀገርን ለመገንባት ሚናው ትልቅ ነው። ይህ የጋራ መግባባት እና ሰላም የማምጣት ሂደት የሀገር በቀል የሽምግልና ሥርዓትም መሠረት ነው።
”ሰማይ ቢቀደድ እንኳ ሽማግሌ ይሰፋዋል” ይላሉ አበው። ይህ አባባል ሽማግሌዎች በልምድ እና በዕውቀት እና በማያወላውል የሰላም ፍላጎታቸው የማይፈቱ ችግሮች እንደሌሉ የሚያሳይ የሕዝባዊ እምነት መግለጫ ነው። ሽማግሌዎች ይመክራሉ፤ ይገስጻሉ፤ ችግሩንም ይፈታሉ።
የአማራ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ ሠብሣቢ መርጌታ ብሩህ ዘላለም የሀገር ሽማግሌዎች በአካባቢያቸው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሽምግልና በመፍታት እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል።
የሰላም ዘላቂነትን ለማረጋገጥ በመመካከር፣ አርቆ በማሰብ እና ችግሮችን በጠረንጴዛ ዙሪያ በውይይት የመፍታት ባሕል በማዳበር እየሠሩ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ሀገር በቀል ዕውቀትን በመጠቀም፤ ግጭቶችን በመቀነስ እና ወገኖች ወደ ሰላም እንዲመጡ በማግባባት ረገድ ሽማግሌዎች ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ እንደኾነም ገልጸዋል። የሽምግልና ጉባኤው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ አካላት የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ በማድረግ የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች የቆዩ እሴቶችን በማሳደግ የማኅበረሰቡ የሰላም ባለቤት እንዲኾን የድርሻቸውን መወጣት ይገባቸዋል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ ምክትል ሠብሣቢ ይመር ሰይድ የሀገር ሽማግሌዎች በባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች አማካኝነት፣ ምንም ዓይነት ወጪ እና ጉልበት ሳይጠይቅ ግጭቶችን በአካባቢ ደረጃ ለመፍታት እየሠሩ እንደሚገኙም አንስተዋል።
በተለይም በደቡብ ወሎ እና በደሴ ከተማ ያሉ ሽማግሌዎች በመተባበር ግጭቶችን አስቀድሞ የመከላከል እና የመፍታት ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
የሀገር ሽማግሌዎች በቅንጅት በአካባቢው ማኅበረሰብ የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በሀገር በቀል ሽምግልና ጉዳዮችን እየለዩ እንደሚፈቱም ነግረውናል።
ሀገር የምታድገው እና የምትለወጠው ሰላም ሲኖር ነው ያሉት አቶ ይመር ለሰላም ግንባታው ሁሉም አካል ትምህርት እና ምክር ሊለግስ ይገባል ብለዋል። በተለይም ከመስጊዶች፣ ከቤተክርስቲያን፣ ከዕድሮች እና በሌሎችም ቦታዎች መሠራት እንዳለበትም ነው ያስረዱት።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
