
ነገ በአዲስ አበባ አንድ ታላቅ አዳራሽ ውስጥ የሀገር ሽታ፣ የባሕል ውበት፣ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ መባባል እና የኢትዮጵያውያን ኅብረ ቀለማት ደምቀው የሚታዩበት አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ይጀመራል።
ከሀገሪቱ ልዩ ልዩ ማዕዘናት የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን ከደጅ አውልቀው ያለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት ለጋራ ዕጣ ፈንታቸው በአንድነት ለመምከር ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው ዋዜማ ላይ ናቸው።
እየተንከባለሉ የመጡ የኢትዮጵያ ችግሮች ውሥብሥብ ቢኾኑም ባለቤቶቹ ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ካልፈቷቸው ማን መጥቶ ይፈታቸዋል? ፈውሱ ያለው በኢትዮጵያውያን እጅ ላይ ነውና መላ የመፈለግ ሂደት ላይ ናቸው።
እንደ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መረጃ ከነገ ጀምሮ የሚደረገው ሀገራዊ ምክክርም ብዙ ውጤት ያመጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። ተስፋው የአንድ ወገን አሸናፊነት ሳይኾን የኢትዮጵያ እና የሕዝቦቿ የጋራ ድል የሚረጋገጥበት፣ ለቀጣዩ ትውልድ የሰላም ውርስ የሚተውበት ታሪካዊ አሻራ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
