ከጦርነት ማን አተረፈ? የአማራ ሕዝብ የሰላም ጥሪ

29
እንግዳ ተቀባይ፤ ሃይማኖተኛ፤ አዛውንቶችን እና ወላጆችን አክባሪ፤ ለሀገሩ ታማኝ፤ የጀግንነት መፍለቂያ፤ የሰላም ተምሳሌት ነው የአማራ ሕዝብ።
ይህ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር፤ ሌሎች የብሔር ወንድሞቹን አቅፎ የያዘ፤ ለጋራ ዕድገት በጋራ ከኢትዮጵያውያን ጋር የሚቆም ነው።
አብሮነት፣ አካታችነት፣ ስለ ሀገር መዋደቅ እና ከወንድሞቹ ጋር በእኩልነት መጓዝ በፍቅር መኖርን ያውቅበታል።
የስብዕና ማማ ባለቤት የኾነው ይህ ሕዝብ ለዘመናት ስለ አብሮነት ተዋድቋል፣ በችግር ወቅት የመነጋገር የመወያየት ባሕሉ ደግሞ በሌሎችም ዘንድ በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው።
አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ የእርስ በእርስ ግጭቶችን በሽምግልና ሥርዓት በውይይት ይፈታል። ይህም ለዘመናት ሰላሙን እና አንድነቱን ጠብቆ እንዲዘልቅ አድርጎታል። የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ ግን በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት ዛሬም እንደቀጠለ ነው።
🚨 ግጭቱ ምን ጉዳቶችን አስከተለ:-በክልሉ ለሦሥት ዓመታት የዘለቀው ግጭት ሕዝብ በነጻነት ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ አድርጎታል። በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል። በሕዝብ በጀት የተሠሩ በርካታ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል። ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመትንም አድርሷል። የንጹሐንን ሕይወትም ቀጥፏል።
በግጭቱ ምክንያት እናት ይጦረኛል ያለችውን ልጅ አጥታለች። ልጅ እናቱን መቅበር ሳይችል ዐይኗ እንደናፈቀው ሳይመለከታት፣ አፈር ሳያለብሳት ቀርቷል። ነብሰ ጡር እናቶች ሆስፒታል ሳይደርሱ መንገድ ላይ ቀርተዋል። ክልሉ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶችን እንዲያስተናግድ አድርጎታል።
🤝ዛሬስ ውይይትን ማድረግ ለምን አቃተው? መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሰላም አማራጭ ጥሪን በተደጋጋሚ አቅርቧል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከ33 ሺህ በላይ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭ መቀበላቸውን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ማስታወቁ ይታወሳል። የአፋሕድን የሰላም ስምምነት ተከትሎም በርካቶች ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን በመቀበላቸው በክልሉ አንጻራዊ ሰላም እንዲገኝ አስችሏል። ዛሬም ያ የሰላም ጥሪ በሩ እንደተከፈተ ነው።
በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሕዝብን ጥቅም አለማስቀደም፤ እውነተኛ ውይይትን አለመፈለግ ግጭቱ እንዲራዘም ማድረጉን መንግሥት በተለያዬ ጊዜ ያወጣቸው መግለጫዎች ያሳያሉ።
🔐 መፍትሄው ምን ይኾን:-ግጭቱ በሕዝብ ላይ ያሳደረውን ጫና መገንዘብ፤ ከጫካ ትግል ይልቅ ወደ ሰላማዊ የውይይት ትግል ማምራት፤ የሕዝብን ጥቅም የማስቀደም፤ ችግሮች በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲፈቱ ማድረግ አማራጭ መንገዶች መኾናቸው በተደጋጋሚ ይጠቀሳል።
የክልሉ መንግሥት የጫካ ትግልን አማራጭ ላደረጉ ታጣቂዎች በተለያዩ ጊዜያት የሰላም ጥሪን እያስተላለፈ ነው።
🤝ለዘላቂ ሰላም የሕዝቡ ሚና ምንድን ነው? የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በደብረ ማርቆስ አየር ማረፊያ ምርቃት ላይ ባደረጉት ንግግር በአማራ ሕዝብ ጥያቄ እየማሉ ሕዝብን የሚያደናግሩ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር የሚሠሩ ታጣቂዎች በመኖራቸው ሕዝቡን ለስቃይ ዳርገውታል ብለዋል።
ሕዝቡ በዘራፊ እና በወንበዴዎች ጉዳት እየደረሰበት በመኾኑ ሰላሙን ሊያጸና ይገባል ነው ያሉት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) በዚሁ ወቅት በደብረ ማርቆስ ባደረጉት ንግግር ለምለም ሀገር ይዘን ተግባብተን፣ ተዋደን ሀገርን መሥራት ሲገባን፤ ባንግባባም ተወያይተን፣ ተነጋግረን ሳንጋደል፣ አብረን መኖር ሲገባን፤ ክፉ ክፉውን የምናስብ መልካሙን የምንገፋ መኾን የለብንም ብለዋል።
በጋራ በመታገል ሕገወጦችን በማጥፋት ሰላም እና ልማትን ማረጋገጥ ያስፈልጋልም ነው ያሉት። ችግሮችን በውይይት በመፍታት፤ በትልቅ ጉዳይ ላይ በመሠብሠብ እና በመተባበር የሁሉም ሰው የጋራ መሻት የኾነውን ሰላም እና ልማት በጋራ ለማስፈጸም መጣር ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
መንግሥት ከሕዝብ ጋር በመኾን ሊወያዩ ሊነጋገሩ የሚፈልጉ አካላትን ለመቀበል የሰላም በሩ ሁሌም ክፍት ነው ብለዋል።
የማያግባቡ ነገሮችን በሰላማዊ እና በሠለጠነ የፖለቲካ አግባብ መነጋገር ይቻላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዛ ውጭ ያለው አማራጭ ኢትዮጵያን አይጠቅምም ነው ያሉት። ግጭት ሊበቃን ይገባል በጋራ መወሰን ያስፈልጋልም ብለዋል።
ከጫካ ትግል ወደ ሰላማዊ ውይይት ለማምራት ከማን ምን ይጠበቃል? እርስዎ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ? ሃሳብዎን በሃሳብ መስጫ ሳጥኑ ላይ ያጋሩን👇👇
#አሚኮ_ዜና#የሰላም_ጥሪ#አማራክልል#ኢትዮጵያ 🇪🇹
#ባሕር_ዳር:ሐምሌ 06/2018 ዓ.ም
በያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እና የአሁኑ ትውልድ ታሪካዊ ኀላፊነት !
Next article“ሕገወጡ የሕወሃት ቡድን ሀገር የማፍረስ ተልዕኮው በግልጽ እየታዬ ነው” አረጋዊ በርሔ (ዶ.ር)