ብሔራዊ ጥቅም የአንድን ሀገር ሕልውና ለመጠበቅ፤ ግዛታዊ አንድነትን ለማስከበር እና የሕዝብን ደኅንነት እና ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ የሚቀረጽ ስትራቴጂካዊ መሥመር ነው።

ውስጣዊ አንድነት ለብሔራዊ ጥቅም
:- በጅንካ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ምስክር ከተማ የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት፣ የልማት ጉዞ እና የሕዝቦቿ ተስፋ በብሔራዊ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ነው ይላሉ።
የማንኛውም ሀገር ጥንካሬ፣ የዲፕሎማሲ የበላይነት እና የብሔራዊ ጥቅም መከበር የሚመነጨው ከውስጥ ሰላም እና አንድነት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም :- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች በሀገር ህልውና እና የወደፊት ተስፋ፤ በልማት ተጠቃሚነት እና በዘርፈ ብዙ ሉዓላዊነት ላይ መሠረት ያደረገ ስለመኾኑም መምህሩ አብራርተውልናል።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር ጠንካራ መንግሥታዊ መዋቅር፤ የተረጋጋ የውስጥ ፖለቲካ እና የማይናወጥ ሕዝባዊ አንድነት ወሳኝ ስለመኾናቸውም ገልጸዋል። ይህም በዓለም መድረክ ያላት የመደራደር እና ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል።

ዓለም አቀፍ ማሳያዎች:-በፖለቲካ ሳይንስ ዕይታ የውስጥ ኃይሎች የእርስ በርስ ግጭት ለውጭ ኃይሎች ተጋላጭነትን ይጨምራል ነው ያሉት። ይህም የውጭ ኃይሎች የራሳቸውን አጀንዳ እንዲያስፈጽሙ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል።
ለዚህም ሶማሊያ፣ ሊቢያ፣ የመን እና የመሳሰሉት ሀገራት በውስጥ አለመረጋጋት እና በፖለቲካ መከፋፈል ምክንያት ለውጭ ኃይሎች መጠቀሚያ ስለመኾናቸው በማሳያነት አንስተዋል።

የመንግሥት ፍላጎት እና ብሔራዊ ጥቅም :- መምህሩ እንደሚሉት የመንግሥት ፍላጎት እና የብሔራዊ ጥቅም ልዩነት ያለው መኾኑን መገንዘብ እና ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል። ብሔራዊ ጥቅም ከመንግሥታት ዕድሜ በላይ የኾነ የሀገርን ዘላቂ ህልውና እና ቀጣይነት የሚያረጋግጥ ስትራቴጂካዊ ጉዳይ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ዜጎች ወይም የፖለቲካ ኃይሎች በሥልጣን ላይ ካለው መንግሥት ጋር የሀሳብ ልዩነት ቢኖራቸው እንኳ በብሔራዊ ጥቅም ላይ በጋራ መቆም እንደሚጠበቅባቸው ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የሉዓላዊነት፣ የኢኮኖሚ እድገት እና የባሕር በር የመሳሰሉ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር በሀገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ልሂቃን እና መላው ዜጎቿ መግባባት መፍጠር ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

በውስጣዊ አንድነት የመጡ ብሔራዊ ጥቅሞች ከታሪክ ተሞክሮ:-ኢትዮጵያ በታሪኳ የውጭ ወራሪዎች እና ከውስጥም ፈተናዎች ሲገጥሟት ሕዝቦቿ የፖለቲካ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው በብሔራዊ ጥቅም እና በሀገር ህልውና ላይ የማይደራደሩባቸው ቀይ መሥመሮች አድርገው ኖረዋል።

ለአብነትም በዓድዋ ድል፣ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ድል እና በዓባይ ግድብ የተገኙት ድሎች እና ስኬቶች ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ መቆምን የሚያስተምሩ የታሪክ አጋጣሚዎች ናቸው ብለዋል።

የአሁኑ ትውልድ ኀላፊነት:-የአሁኑ ትውልድም ይህንን የታሪክ እውነት በመድገም የሀገሪቱን የውስጥ ሰላም በመጠበቅ የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ እና ሌሎችንም የብሔራዊ ጥቅሞቿን የማስከበር ታሪካዊ ኀላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።


እርስዎስ ምን ይላሉ?
በሀገራዊ ጥቅሞች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ከልሂቃን እና ከዜጎች ምን ይጠበቃል? አስተያየትዎን ያጋሩን


።

በአሰፋ ልጥገበው